በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር የ12ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ በቅድሚያ የተደረገው የመከላከያ እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ አንተነህ ጉግሳ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ የጦና ንቦቹ አሸንፈው ወጥተዋል።
መከላከያዎች በ11ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ አስራአንድ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ብቻ በማድረግ የገቡ ሲሆን በልደቱ ጌታቸው ምትክ ኢብራሂም መሀመድ የመሰለፍ ዕድል ያገኘ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል አዲስ አበባ ከተማን ካሸነፉበት ጨዋታ ሁለት ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን አዲስ ህንፃ እና አናጋው ባደግ ፤ እንድሪስ ሰይድን እና ምንይሉ ወንድሙን ተክተው ጨዋታውን እንዲጀምሩ እደርገዋል ።
ከድል መልስ ወደዚህ ጨዋታ የመጡተን ሁለቱን ክለቦችን ያገናኘው ግጥሚያ ግብ ለማስተናገድ ሰባት ደቂቃዎች ነበር የፈጁበት ። የግቡ ባለቤቶች የጦና ንቦቹ ሲሆኑ ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ አዲስ ህንፃ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ለአንተነህ ጉግሳ ያደረሰውን ኳስ አንተነህ ተረጋግቶ ግብ በማድረግ ክለቡን መሪ አድርጓል ። ግብ ያስተናገዱት መከላከያዎች ከዚህ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች ላይ ብልጫ በመውሰድ ለመጫወት ሞክረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ምንም እነኳን በተሻለ ለወደፊት መሄድ ቢችሉሜ በጨዋታው ጥሩ የነበረውን የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር ለማስከፈት የተቸገሩት መከላከያዎች ከቆሙ ኳሶች እና ከርቀት በሚመቱ ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል ። 14ኛ ደቂቃ ላይ ብሩክ ሰሙ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ወንድወሰን አሸናፊ ለጥቂት ግብ ከመሆን የዳነ ሲሆን 20ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ ግሩም ሀጎስ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳሱ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል ።
በአጋማሹ በሁለቱም በኩል ኳሶች በተደጋጋሚ ከኋላ ወደ ፊት በረጃጅም ሲላኩ የነበረ ሲሆን ሌላ ጠንከር ያለ ሙከራ ሳይታይ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ችሏል ።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ተጭነው በመጫወት የጀመሩት ሲሆን በተለይም በግራ መስመር የነበረው ቢንያም በላይ ወደ ግብ ክልል በሚያሻግራቸው ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም በጨዋታው በጥሩ ቅንጅት ሲጫወት በነበረው የወላይታ ድቻ የተከላካይ ክፍል ሲከሽፉባቸው ነበር ። በወላይታ ድቻ በኩል በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ በተፈጠረባቸው ወደ መከላከሉ አድልተው የነበረ ቢሆንም ቀስ በቀስ መነቃቃት በማሳየት በፈጣን ሽግግሮች ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራ ለማድረግ አልቻሉም ።
በ47ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ህንፃ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ አንተነህ ጉግሳ በግንባር መግጨት ቢችልም ሙከራው ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ሊወጣ ችሏል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ መከላከያዎች በግራ መስመር በኩል ያገኙትን የቅጣት ምት ግሩም ሀጎስ ወደ ግብ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ወንድወሰን አሸናፊ አድኖበታል ።
ጨዋታው 60ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቢንያም በላይ ከመስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ተሾመ በላቸው አግኝቶ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የመለሰቀት ሲሆን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ኳሶችን ቶሎ ቶሎ የመነጣጠቅ እና በፈጣን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የበዙበት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢታይም ክሌመንት ቦዬንም ሆነ ወንድወሰን አሸናፊን የፈተኑ የግብ ሙከራዎች ሳይደረጉ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ ነጥቡን 22 በማድረስ ከፋሲል ከተማ ጋር በነጥብ የተስተካከለ ሲሆን በግብ ክፍያ ተበልጦ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን መከላከያ በ14 ነጥብ ባለበት 11ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መከላከያ አዳማ ከተማን ወላይታ ድቻ ደግሞ ጅማ አባጅፋርን የሚገጥሙ ይሆናል ።