በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና መከላከል መካከል ተደርጎ በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ወላይታ ድቻዎች በ26ኛው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በተረቱበት ጨዋታዉዋይ የነበረውን ምርጥ 11 ሙሉ ለሙሉ ሲጠቀሙ በመከላከያ በኩል በሳምንቱ ከወልቂጤ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ኢብራሂም ሁሴን እና ግሩም ሀጎስን በገናናው ረጋሳ እና ኢማኑኤል ላርዬ ምትክ አሰልፈዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ወላይታ ድቻዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን መከላከያዎች የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጥጥ ሞክረዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ቀዳሚ የነበሩት የጦና ንቦቹ ሲሆኑ ቃልኪዳን ዘላለም በረጅም የደረሰውን ኳስ እየገፋ ይዞ በመግባት ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ቃልኪዳን ከቅጣት ምች የደረሰውን ኳስ ግብ ለማድረግ ያደረገው ጥረት በተመሳሳይ ሳይሳ ቀርቷል ።
ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረቶችን ያደረጉት መከላከያዎች በተለይም ከግራ መስመር በቢንያም በላይ በሚነሱ ኳሶች የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ችለዋል ። በዚህም 12ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ከግራ መስመር ተነስቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ ኢላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ተሾመ በላቸው ከቢንያም በላይ የደረሰውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ወደ ግብ የላከው ጠንካራ ኳስ ወደ ዉጪ በጥቶበታል ።
በ24ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች ቀዳሚ መሆን የሚችሉበትን ወርቃለማ ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። ክሌመንች ቦዬ ከራሱ የግብ ክልል በረጅም የመታው ኳስ የወላይታ ድቻን ተከላካይ አልፎ የደረሰው እስራኤል እሸቱ ኳሱን እየገፋ ሄዶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሳያስቆጥረው ቀርቷል ።
የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ሙከራም በመከላከያ በኩል ሲደረግ አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መከላከያዎች የተሻለ በመንቀሳቀስ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም የተሳካ የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል አልፈው ጠንካራ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር አንፃር የተሳካ ጊዜን አላሳለፉም ። በአንፃሩ በወላይታ ድቻ በኩል በአጋማሹ በተወሰደባቸው አንፃራዊ ብልጨሠ ዘደ ኋላ ለማፈግፈግ ቢገደዱም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ችለው ነበር ።
በ53ኛው ደቂቃ ላይም ከማዕዘን በተነሳ ኳስ በአዲሩ አቱላ ተጨርፎ ሲመለስ ያገኘው ደጉ ደበበ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል ።
በሙከራዎች ረገድ ልክ እንደአየሩ ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለው ጨዋታ ቀጣዩን የግብ ሙከራ በ85ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ያስመለከተን ። በዚህም ስንታየሁ መንግሥቱ ከቃልኪዳን ዘላለም የደረሰውን ኳስ ዞሮ ወደ ግብ መመኮር ቢችልም ኳሱ በክሌመንት ቦዬ ተይዟል ።
ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ38 ነጥብ በ6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥል መከላከያ በበኩሉ ነጥቡን 32 በማድረስ ወደ 8ኛ ከፍ ማለት ችለዋል።
በ28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 16 ( ሐሙስ ) ረፋድ 4:00 ወላይታ ድቻ ጅማ አባጅፋርን ሲገጥም መከላከያ በበኩሉ ሰኔ 17 ( አርብ ) ከሲዳማ ቡና የሚጫወት ይሆናል ።