የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንት መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ ወላይታ ድቻን ሁለት ለዜሮ በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
አስቀድሞ በተያዘለት መርሐግር በዛሬዉ ዕለት ረፋድ 4:00 ሰዓት ሲል የተጀመረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በአጨዋወት ረገድ የወልቂጤ ከተማዎችን የበላይነት የተመለከትን ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ዲቻዎች ደግሞ አብዝሀኛዉን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በራሳቸዉ የሚዳ ክልል ላይ በመቆየት በይበልጥ ጥንቃቄ ላይ ያተኮረን የጨዋታ መንገድ ሲከተሉ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት ጅማሮዉን ባደረገዉ የሁለቱ ቡድኖች የአመቱ የመጨረሻ ጨዋታም በ19ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ የሚባል ሙከራን አስመልክቶናል። በዚሁ ደቂቃ ላይም የክትፎዎቹ የፊት መስመር አጥቂ ጌታነህ ከበደ ወደ ግራ ካደላ ቦታ ላይ ቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ የሞከራት ኳስ በግቡ አናት ላይ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
- ማሰታውቂያ -
ከዚች ሙከራ በኋላ እምብዛም የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ያልተመለከትናቸዉ ዲቻዎች በ23ኛዉ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ማድረግ ችለዋል። ከቀኝ መስመር በኩል ከከንዓን ከበደ የተቀበለዉን ኳስ አበባየሁ አጪሶ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ በድጋሚ የግቡን አግዳሚ ታካ ወጥታለች።
ከደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አበባየሁ በድጋሚ ጥሩ ዕድል አግኝቶ ወደ ግብ ቢሞክርም የግብ ዘቡ ሮበርት ኦዶንካራ አዉጥቶታል። በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የመጀመሪያው አጋማሽ ምንም እንኳን ተመጣጣኝ የጨዋታ ፉክክርን የተመለከትንበት ቢሆንም በሙከራ ረገድ ግን በጥቂቱም ቢሆን የተቀዛቀዘ የመጀመሪያ አጋማሽ ነበር ማለት ይቻላል።
ከዕረፍት መልስ በተለይ የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች እንደ መጀመሪያዉ አጋማሽ ሁሉ በተመሳሳይ የጨዋታ ምንገድ በቀጠለዉ የሁለቱ ክቦች ጨዋታም አጋማሹ ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ ግን ግብ ተስተናግዶበታል። በዚህም በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ አክሊሉ ዋለልኝ ከቀኝ መስመር በኩል የሻገረዉን ኳስ ተቀይሮ የገባዉ ቤዛ መድህን ወደ ግብነት ቀይሮ ወልቂጤ ከተማዎች እንዲመሩ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ አቻ ለመሆን ጥረት ማድረግ የጀመሩት ዲቻዎች አስቀድሞ ሲተገብሩት የነበረዉን የጨዋታ መንገዳቸው ላይ ለዉጥ አድርገዉ በይበልጥ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመጠጋት ኳሶችን ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት በመላክ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም ነበር። በተለይ በ78ኛዉ ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ በረጅሙ የቸሻገረን ኳስ ቢንያም ፍቅሬ ከተቆጣጠረ በኋላ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ የግብ ዘቡ ሮበርት ደርሶ ያዳነበት ሙከራ በዲቻዎች በኩል አስቆጬ ሙከራ ነበረች።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በሔደ ቁጥር በተመሳሳሳ ጨዋታዉ እየቀዘቀዘ ሄዶ ሊጠናቀቅ የዳኛዉ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት በ90ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ሳይጠበቅ ክትፎዎቹ ተጨማሪ ግብ ማግኘት ችለዋል። በዚህም ከመሐል ክፍል በረጅሙ የተሻገረዉን ኳስ የዲቻ ተከላካዮች ለመቆጣጠር በሚሞክሩበት ሰዓት በተፈጠረዉ አለመግባባት በአቅራቢያዉ የነበረዉ አጥቂዉ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብነት ቀይሮ አጠቃላይ በዉድድር አመቱ ያስቆጠራቸዉን ግቦች ወደ 14 ከፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን በተመሳሳይም ክለቡ ወልቂጤ ከተማ ጨዋታዉን 2ለ0 እንዲያሸንፍ ማድረግ ችሏል።