ቀን ሰባት ሰዓት ላይ በተደረገዉ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 3ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በእንቅስቃሴ ደረጃ በተለይ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ያህል የድሬዳዋ ከተማዎችን የበላይነት በተመለከትንበት ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ መሪ መሆን ችሏል። ምንም እንኳን በርቱካናማዎቹ ብልጫ ተወስዶባቸዉ የነበሩት አዞዎቹ በ14ኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻማውን ኳስ አህመድ ሁሴን በጭንቅላቱ በመግጨት ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ለመቀጠል ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ድሬዳዋ ከተማዎች 30ኛዉ ደቂቃ ላይ አቻ ሊሆኑ የተቃረቡበትን ዕድል አጊኝተዉ የነበረ ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በዚህ ደቂቃ ላይም የመስመር ተጫዋቹ አቤል ከበደ ወደ ግብ የሞከረዉን ኳስ የአርባምንጩ ግብ ጠባቂ ሲመልሰዉ አጥቂው ማማዱ ሲዲቤ አግኞቶ ቢሞክርም ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል።
- ማሰታውቂያ -
በተለይ የመሐል ሜዳዉን በበላይነት ለመቆጣጠር ሲሞክሩ የነበሩት አዞዎቹ ምንም እንኳን ዉጤታማ ባይሆንም በተደጋጋሚ ለአጥቂው አህመድ ሁሴን ረዣዥም ኳሶችን በመጣል ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ሲጥሩ ተስተውሏል። በዚህም በአጋማሹ መገባደጃ 44ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ ያደረጉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
ከማዕዘን የተሻገረዉን ኳስ ለማፅዳት ሲሞክሩ የድሬዳዋ ከተማዎች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የገኘዉን የፍፁም ቅጣት ምት ኤሪክ ካፓይቶ በማስቆጠር ድሬዳዋ ከተማ ሁለት ለዜሮ እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል እዲያመሩ ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ብርቱካናማዎቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በ56ኛዉ እና 60ኛዉ ደቂቃ ላይ በአጥቂዉ ማማዱ ሲዲቤ እና አቤል ከበደ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በተደጋጋሚ የጨዋታ ብልጫ በመዉሰድ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ድሬዳዋዎች ተሳክቶላቸዉ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ሶስተኛ ግብ አስተናግደዋል። በ70ኛዉ ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማዉ ተከላካይ መሳይ ጳዉሎስ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘዉን የፍፁም ቅጣት ምት ኤሪክ ካፓይቶ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡ 3ለ0 በሆነ ዉጤት አሸንፎ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል።
ዉጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ በ37 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ29 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።