በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአስረኛ ሳመንት ቀዳሚ ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ የተደረገው የድሬዳዋ ከተማ እና የመከላከያ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት በተጫወተው ድሬዳዋ ከተማ የ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ድሬዳዋ ከተማ በዘጠነኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ አዲስ አበባን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሰባት ያህል ቅያሪዎችን አድርገው የገቡ ሲሆን ፍሬው ጌታሁንን ፤ ሄኖክ ኢሳይያስን ፤ ዳንኤል ሀይሉን ፤ ዳንኤል ደምሴን ፤ አብዱልፈታ ዓሊን ፤ አብዱራህማን ሙባረክን እና ማማዱ ሲዲቤን በደረጄ አለሙ ፤ ብሩክ ቃልቦሬ ፤ መሀመድ አብዱለጢፍ ፤ ሱራፌል ጌታቸው ፤ መጣባቸው ሙሉ ፤ ጋዲሳ መብራቴ እና አቤል ከበደ ቀይረው አስገብተዋል ። በመከላከያ በኩል ደግሞ በፋሲል ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ኢማኑኤል ላርያ ፤ ብሩክ ሰሙን እና ሰመረ ሀፍተይን በዳዊት ወርቁ ፤ ቢንያም ላንቃሞ እና ላርዬ ኢማኑኤል ተክተው አስገብተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ያስመለከት ነበር ። በድሬደዋ ከተማም ሆን በመከላከያ በኩል ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት ያለበት የጨዋታ ሂደት በሜዳ ላይ ብንመለከትም ወደ ግብ ቀርቦ የግብ ሙከራ በማድረጉ ረገድ በሁለቱም በኩል ድክመቶች ነበሩ ።
24ኛው ደቂቃ ላይ አብዱራህማን ሙባረክ በቀኝ መስመር በኩል በረጅም የተላከለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ይዞ ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ በክሌመንት ቦዬ መረብ ላይ አርፎ ድሬዳዋን መሪ አድርጓል ።
ከግቡ በኋላ መከላከያዎች ቀድሞ ከነበረው ጥሩ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ ሲሆን በተለይም ከምዕዘን ከቢንያም በላይ በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም በግብ ጠባቂ በመመለስ እና ከኢላማ ውጪ በመሆን ግብ መሆን አልቻሉም ። በተለይም 45ኛ ደቂቃ ላይልደቱ ጌታቸው ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ፍሬው ጌታሁን ጨርፎት ከኋላው የነበረው መሳይ ጳውሎስ ያወጣው ኳስ ለመከላከያዎች አስቆጪ ነበር ።
በሁለተኛው ኢጋማሽ ጅማሮ በመመራት ላይ የነበሩት የዮሀንስ ሳህሌ ተጫዋቾች ቀደም ብሎ ከነበራቸው እንቅስቃሴ በተሻለ ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ። በአንፃሩ በደጋፊዎቻቸው ፊት የሚጫወቱት ድሬዳዋ ከተማዎች በረጃጅም ኳሶች እና በፈጣን መልሶ ማጥቃች የግብ ዕድሎችን ለማግኘት ሲሞክሩ ተስተውሏል ።
48ኛ ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ከሳጥኑ በቅርብ ርቀት ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወቷል ። መከላከያዎች በግራ መስመር በተለይም በቢንያም በላይ አማካኝነት ተጭነው በመጫወት ወደ ግብ ለመቅረብ ያደረጓቸው ጥረቶች በቀላሉ በድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች ይከሽፉባቸው ነበር ።
ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለው ጨዋታ ወደ መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የሚሄዱ ሷሶችን አስመልክቶናል ። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን በረጅም የመታውን ኳስ ሄኖክ አየለ በጭንቅላት ገጭቶ ለአብዱራህማን ሙባረክ ቢያቀብለውም አብዱራህማን ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ለጥቂች ወደ ውጪ ወቷል ። እንዲሁም በጨዋታ እንቅስቃሴ እና በቆመ ኳስ በሙኽዲን ሙሳ እና ዳንኤል ሀይሉ የተደረጉት ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ክሌመንት ቦዬ አማካኝነት ግብ ከመሆን ድነዋል ።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት 90+4ኛ ደቂቃ ላይ አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውስጥ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በቀላሉ በፍሬው ጌታሁን ተይዟል ። በስተመጨረሻም ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታውን አሸንፎ አጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ድሬዳዋ ከተማ ነጥቡን 14 በማድረስ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ሲል መከላከያ በ11 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።