የመውረድ ስጋት ውሰጥ ያሉት ሁለቱ ክለቦች አመሻሽ 12 ሰዓት ጀምሮ ያደረጉት ጨዋታ ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴዎች የተጀመረ ነበር ። በድሬዳዋ ከተማም ሆነ በሰበታ ከተማ በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎችንም መፍጠር ችለዋል ።በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 15ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን ሙከራውም ወደ ግብነት መቀየር የቻለ ነበር ። አቤል አሰበ ከሳጥኑ ውጪ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በምንተስኖት አሎ መረብ ላይ አርፎ ብርቱካናማዎቹን ቀዳሚ አድርጓል ።
ከግቡ በኋላ ሰበታ ከተማዎች በጨዋታው ላይ ብልጫ ወስደው በመጫወት የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረቶችን አድርገዋል ። በተለይም 17ኛው ደቂቃ ላይ ዴሪክ ንስምባቢ ያገኘውን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል በፍሬው ጌታሁን ተመልሶበታል ። በ22ኛው ደቂቃ ላይ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ማማዱ ሲዲቤ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሄኖክ አየለ በግንባር መግጨት ቢችልም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅለት ቀርቷል ።
በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ሰበታ ከተማዎች በተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ሙከራን ማድረግ ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች የማጥቃት ኃይላቸውን በተጫዋቾች ቅያሪ በማጠናከር የፍሬው ጌታሁንን መረብ ለመድፈር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በሰበታ ከተማ በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳው የፊት መስመር ክፍተት በዚህ ጨዋታም ቀጥሎ የታየ ነበር ።የድሬዳዋ ከተማው ተከላካይ ያሲን ጀማል በበሀይሉ ግርማ ለይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊሰናበት ችሏል ።
- ማሰታውቂያ -
የድሬዳዋ ከተማን በቁጥር መጉደል ለመጠቀም በቁጥር በዛ በለው በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ላይ መገኘት የቻሉት ሰበታ ከተማዎች ኳስ እና መረብን የሚያዋህድላቸው ተጫዋች ለማግኘት ግን አልቻሉም ነበር ።በድሬዳዋ ከተማ በኩል በመከላከሉ ተጠምደው በመቆየት በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሌላ ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ሙከራ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። ሄኖክ አየለ ከግራ የሳጥኑ አቅጣጫ ከመሀመድ አብዱለጢፍ የደረሰውን ኳስ በሰበታ ከተማ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን 2 – 0 እንዲመራ ማድረግ ችሏል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።