በ17ኛው ሳምንት የሶሰተኛ ቀን ውሎ የመጀመሪያ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና በሲዳማ ቡና መካከል ተደርጎ ግብ ሳይቆጠርበት 0 – 0 ተጠናቋል ።
ድሬዳዋ ከተማ በ16ኛው ሳምንት በወላይታ ድቻ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ መሀመድ አብዱለጢፍ ፤ አቤል አሰበ እና አቤል ከበደን በአማረ በቀለ ፤ ዳንኤል ሀይሉ እና ሙኽዲን ሙሳ ተክተው ያስገቡ ሲሆን በሳምንቱ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ የተጋሩት ሲዳማ ቡናዎች በጨዋታው ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ብርሀኑ አሻሞን በሙሉአለም መስፍን ምትክ አስገብተዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ያን ያህል ሙከራዎች ያልታዩበት እና በሁለቱም በኩል የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል ለማስከፈት ያደረጎቸው ጥረቶች ውጤታማ ያልነበሩበት ነበር ።
ሲዳማ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ቢሆኑም የድሬዳዋ ከተማ የኋላ መስመር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ከባድ ሆኖባቸው ነበር። በአጋማሹም በሁለት አጋጣሚዎች ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው የነበረ ሲሆን 12ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሙሉጌታ ከዳዊት ተፈራ ጥሩ ኳስ ደርሶት ተከላካዮችን አልፎ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ፍሬው ኳሱን መልሶበታል ። ሌላኛው ደግሞ የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ይገዙ ቦጋለ ያደረገው ሙከራ ሲሆን ከቀኝ መስመር በኩል ከደግፌ አለሙ የደረሰውን ኳስ በቀላል ምት ወደ ግብ ልኮት ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል ።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል ጋዲሳ መብራቴ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በተክለማርያም ሻንቆ ከተያዘበት ውጪ ሌላ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ነበር አጋማሹን ያጠናቀቁት ።በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ሲዳማ ቡናዎች አንጋፋውን አጥቂ ሳልሀዲን ሰይድን በብሩክ ሙሉጌታ ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት ከይገዙ ቦጋለ ጋር አጣምረው ግብ ለማግኘት ጥረቶችን አድርገዋል ። አጋማሹ ከመጀመሪያው በተሻለ ኳሶች ወደ ግብ ክልል የሚደርሱበት እና በተለይም በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ጠንከር ጠንከር ያሉ የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
ድሬደዋ ከተማዎች በ47ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን መፍጠር የቻሉ ሲሆን አቤል አሰበ ከጋዲሳ መብራቴ የተሰነጠቀለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በተክለማርያም ሻንቆ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።በ52ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ፍሬው ሰለሞን ሲያሻግረው የመሀል ተከላካዩ ጊት ጋትኩት በግንባር ገጭቶ መሞከር ቢችልም ኳሱ ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል ቀርቶ ወደ ውጪ ወቷል ።
ሲዳማ ቡናዎች በቀኝ መስመር በኩል በማድላት የድሬዳዋ ከተማን ግብ ለማግኘት የጣሩ ሲሆን ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ሳልሀዲን ሰይድ በ63ኛው ደቂቃ ላይ ጠንካራ ሙከራ አድርጎ በፍሬው ጌታሁን ተመልሶበታል ። ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላም በዚሁ አቅጣጫ ይገዙ ቦጋለ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስም በድጋሚ በፍሬው ተይዟል ።ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ ጫና በመፍጠር ወደ ግብ ለመድረስ ቢጥሩም የድሬዳዋ ከተማ የኋላ መስመር ወደ ሳጥን ገብተው የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል ። 83ኛው ደቂቃ ላይም ፍሬው ሰለሞንን ቀይሮ የገባው ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውጪ ያደረገው የግብ ሙከራ ቀደም ብለው እንደነበሩት ሙከራዎች የድሬዳዋ ከተማውን ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁንን ማለፍ የቻለ አልነበረም ።
በመጨረሻም ጨዋታው በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ግብ ሳያሰተናግድ ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 27 አድርሶ ከፋሲል ከተማ ጋር መስተካከል ቢችልም በግብ ልዩነት ተበልጦ በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት የተገደደ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማም ነጥቡን 17 ማድረስ ቢችልም ከ13ኛ ደረጃ መንቀሳቀስ አልቻለም ።
በ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ በመጪው ሰኞ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ሲዳማ ቡና በበኩሉ ከሁለት ቀናት በኋላ በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል ።