ፈረሰኞቹ በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እየተመሩ ኢትዮጵያ መድንን 7ለ1 በሆነ ዉጤት ካሸነፉበት የመጀመሪያው ሳምንት ጨዋታ ምንም ለዉጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተቃራኒው ኤሌትሪኮች በባህርዳር ከተማ በሊጉ የመክፈቻ ቀን የ1ለ0 ሽንፈትን ካስተናገዱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለዉጥ አድርገዉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የመጀመሪያ 20 ያህል ደቂቃዎቹን በሙከራ ረገድ ቀዝቃዛ በነበረዉ በዚህ ጨዋታ በንፅፅር ብልጫ የነበራቸዉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም እንኳን ተጠቃሽ ሙከራ አያድርጉ እንጅ በተጋጣሚያቸዉ ላይ በተለይ በሜዳዉ ሶስተኛ ክፍል ጥሩ ነበሩ ማለት ይቻላል። በዚህም በ27ኛዉ ደቂቃ ላይ አማካዩ ዳዊት ተፈራ ከመስመር ተጫዋቹ ቸርነት ጉግሳ የተቀበለዉን ኳስ ሳይጠቀምባት የቀረዉ አጋጣሚ ተጠቃሽ ሲሆን ፤ በድጋሚ በ29ኛዉ ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከሳጥኑ ዉጭ ወደ ግብ የላካት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ናት ።
- ማሰታውቂያ -
በተቃራኒው በፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢወሰድባቸዉም በተደራጀ መልኩ በመንቀሳቀስ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ኤሌትሪኮች በሂደት ወደ ጨዋታዉ ተመልሰዉ በ36ኛዉ ደቂቃ ላይ ድንቅ ሙከራን ማድረግ ችለዋል። በዚህም የፊት መስመር ተጫዋቹ ሄኖክ አየለ ከኢብራሂም ከድር የተሻገረለትን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢሞክርም በተከላካዩ ደስታ ደሙ ተመልሶበታል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም አጋማሹ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በተሻለ የጨዋታ ዘይቤ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኢብራሂም ከድር አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ የነበረ ቢሆንም የመስመር ተጫዋቹ ፀጋ ደርቤ በዕጅ ነክቷል በሚል ጎሉ ተሽሯል።
በእንቅስቃሴ ረገድ እየተሻሻሉ የሄዱት ፈረሰኞቹ በፊት መስመር አጥቂያቸዉ ኦሮ አጎሮ አማካኝነት በ57ኛዉ ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራን አከታትለዉ ማድረግ ችለዋል። በዚህም አጥቂዉ ከአማካዩ ዳዊት ተፈራ የተቀበለዉን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷ ለጥቂት ወጥታለች። በተጨማሪም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ አጎሮ ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም በኤሌክትሪኩ የግብ ዘብ ኳሷ ግብ ከመሆን ከሽፋለች።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በሄደ ቁጥር ጫናቸዉን ይበልጥ የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በ77ኛዉ እና በ81ኛዉ ደቂቃ ላይ በኦሮ አጎሮ እና በመስመር ተጫዋቹ ተከታታይ ሙከራን ማድረግ ቢችሉም ግብ ለማስቆጠር ግን የግድ የዳኛዉን ጭማሪ ሰዓት መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። በዚህም በ93ኛዉ ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን የሱፍ ያሻገረዉነ ኳስ አምበሉ ፍሬምፖንግ ሜንሱ በጭንቅላት በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን ጣፋጭ ድል እንዲጎናፀፉ አድርጓል።
በቀጣይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና ጋር የሚገናኝ ሲሆን በተቃራኒው ኢትዮ ኤሌትሪክ ደግሞ ከወላይታ ድቻ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።