ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን በዋና ዳኛ በላይ ታደሰ እየተመሩ ረፋድ 3:00 ላይ ሲጀምሩ ሁለቱም ክለቦች በእኩል ሶስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠዉ በሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸዉ ደግሞ ጨዋታዉ ይበልጥ እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር።
በጨዋታዉም ኮልፌ ቀራኒዮ ይበልጥ መሀል ክፍሉ ላይ ኳስን ተቆጣጥረው በመጫዎት ወደግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል በዚህ አጨዋወታቸውም በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል መድረስ ችለዉ ነበር።
በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመስመር ተጫዋቾቻቸዉ ኤርሚያስ ሀይሉ እና አደም አባስ ወደ ግብ ለመድረስ ያድርጉት የነበረዉ ጥረት ስኬታማ አልነበረም።
ከእረፍት በኋላ ይበልጥ ተጠናክረዉ የቀረቡት ኮልፌዎች በብሩክ ሙልጌታ እና ሀቢብ ከማል ለግብ የቀረቡ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።
- ማሰታውቂያ -
ሙከራቸዉም ፍሬ አፍርቶ በ63ኛዉ ደቂቃ በብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ መምራት ጀመሩ ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት ኤሌክትሪኮች በተደጋጋሚ ተቀይሮ በገባዉ ፀጋ ደርቤ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ቢያደርጉም ማስቀጠር ሳይችሉ ቀርተዉ በ81ኛዉ ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾችን ስህተት በሚገባ ተጠቅሞ የኮልፌዉ አብዱሰላም የሱፍ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ቻለ።
በዚህም መሰረት ኮልፌ ቀራኒዮ ኤሌክትሪክን 2ለ0 በመርታት ወደ ሊጉ ለማደግ የሚያደርጉት ጉዞ ሲያሳምሩ በአንፃሩ የክፍሌ ቦልተናዉ ኢትዮኤሌክትሪክ አጣብቂኝ ዉስጥ ገብቷል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ኮልፌ ቀራኒዮ:- አሰልጣኝ መሀመድ ኑር
ከሜዳ ውጪ ቡድኑ ላይ ስለተፈጠረዉ ጫና?
ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ጥሩ ከሆነ የትኛዉም ክለብ እይታ ዉስጥ መግባት እንደሚችሉ በትላንትናው ዕለት ከተጫዋቾቹ ጋር በመነጋገር እና በመወያየታችን ሜዳ ላይ ትልቅ ዉጤት ማግኘት ችለናል።
ቡድኑ ወደ ጨዋታ ስለተመለሰበት መንገድ?
በመጀመሪያ ተጋጣሚያችን ኤሌክትሪክ ትልቅ ቡድን ነዉ ፈልገዉት የነበረዉም በራሳቸው ሜዳ በመጫወት እኛን ስበዉ በካውንተር ለመጠቀም ነበር ያሰቡት እኛም ይሄን ተገንዝበን እነሱ በሚሳሳቱት ኳስ አጊኝተን ለመጠቀም ያደረግነው ጥረት ፍሬያማ ነበር።
የቡድኑ እንቅስቃሴ አጥጋቢ ነበር?
በእንቅስቃሴ ረገድ እንደከዚህ ቀደሙ ጥሩ ባንሆንም ነገር ግን ዉጤቱን ፈልገነዉ ስለነበር ትኩረታችን ነጥብ ይዞ ለመዉጣት ነበር።
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ:- አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና
የነበራቸው የጨዋታ ብልጫ ማስቀጠል ስላለመቻላቸዉ?
የማሸነፍ ፍላጎታቸው ጫና ፈጥሮባቸዋል ብየ አስባለሁ ቢሆንም ግን ካለፋት ጨዋታዎች አንፃር እንደ ቡድንም እንደ ግልም ጥሩ አልነበርንም። ተጋጣሚያችን ደግሞ በተቃራኒው እንደቡድን ጥሩ ነበሩ የኛን ስህትትም መጠቀም ችለዋል።
ከዚህ በኋላ ወደ ዉጤታማነት ስለመመለስ?
አንድ አንድ ለዉጦችን አስተካክለን ወደ ዉጤታማነት እንመለሳለን ብየ አስባለሁ። ዛሬም እንዳየነዉ ተቀያሪ ላይ የነበሩት ልጆች ጥሩ ነበሩ በቀጣይም እነዚህን ልጆች ወደ አሰላለፍ በማምጣት ጥሩ ነገር ለመስራት እናስባለን።
ደረጃ ሰንጠረዥ