በዕለቱ ሁለተኛ የጨዋታ መርሀግብር ኢትዮጵያ ቡና እና ወልቂጤ ከተማ ከ10:00 ጀምሮ ጨዋታቸውን አድርገው መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አስራ ሶስት ያህል ደቂቃዎች እስኪቀሩት ድረስ 3 – 1 በሆነ ውጤት ሲመሩ የነበሩት ቡናማዎቹ በመጨረሻም 4 – 3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ጣፋጭ ድል አስመዝግበዋል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በሳምንቱ ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱ የነበረውን የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ በዮናታን ፍስሀ እና አቡበከር ሳኒ ምትክ ተስፋዬ ነጋሽን እና ዮናስ በርታን ተክተው ገብተዋል ።
የኢትዮጵያ ቡና እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ የሰዓት መቁጠሪያው በሰከንዶች ዕድሜ ሳለ ነበር ቀዳሚውን ግብ ያስተናገደው ። ታፈሰ ሰለሞን ለአበበ ጥላሁን ለማቀበል የሞከረውን ኳስ አበበ ጥላሁን መቆጣጠር ሳይችል በቀረበት አጋጣሚ ጫላ ተሺታ ወደ ግብ ይዞ በመሄድ ሰራተኞቹን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ወልቂጤ ከተማ ሳጥን ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ። በአንፃሩ በወልቂጤ ከተማ በኩል የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅም ለጫላ ተሺታ እና ጌታነህ ከበደ በማድረስ ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ6ኛው ደቂቃ ላይ የቡናማዎቹ የኳስ ቅብብል ወደ ሳጥን ገብቶ ሀብታሙ ሸዋለም ኳሱን ለማራቅ ባደረገው ጥረት ኳሱ የደረሰው አብነት ደምሴ ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል ።
ቡናማዎቹ ኳሱን ይዘው ክፍተቶች ለማግኘት ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሳሉ ሌላ ግብ አስተናግደዋል ። ጌታነህ ከበደ ያብቃል ፈረጃ የሰራበትን ጥፋት ተከትሎ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ መግቢያ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ራሱ መቶ አስቆጠሯል።
25ኛው ደቂቃ ላይ በታፈሰ ሰለሞን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ሀይሌገብረትንሳይ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ በሮበርት ኦዶንግካራ ተይዞበታል ።
ጨዋታው ከውሀ እረፍት መልስ ሲቀጥል አስራት ቱንጆ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ ኳስ ለማቀበል በሚጥርበት ሰዓት በሀይሉ ተሻገር በእጅ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አቡበከር ናስር ከመረብ አሳርፎ የኢትዮጵያ ቡናን የመጀመሪያ ግብ 30ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ።
ሰራተኞቹ ከቡናማዎቹ ተከላካዮች ጀርባ ኳሶችን በመጣል ወደ ፊት ለመድረስ ቢጥሩም በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ይሆኑ ነበር ።
36ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች መሪነታቸውን ከፍ ያደረጉበትን ግብ አግኝተዋል ። ጌታነህ ከበደ ከሀብታሙ ሸዋለም የደረሰውን ኳስ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ላይ በመግባት ወደ ግብ የመታው ኳስ በበረከት አማረ መረብ ላይ አርፏል ። ይህም ግብ ጌታነህ ከበደን በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት 11 በማድረስ ለደቂቃዎች የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃውን ለብቻው እንዲመራ አስችሎታል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በወልቂጤ ከተማ የ3 – 1 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ቡናማዎቹ በተሻለ ወደ ወልቂጤ ከተማ የግብ ክልል መድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ። በተለይም በግራ መስመር አቅጣጫ ላይ አመዝኖ የሚደረገው የቡናማዎቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች ፈታኝ ነበር ። በወልቂጤ ከተማ በኩል መከላከሉ ላይ በማተኮር በፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል ።
በአጋማሹ ቀዳሚ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ
50ኛው ደቂቃ ላይ በታፈሰ ሰለሞን የተደረገ ሲሆን ከአማኑኤል ዮሐንስ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ሞክሮ ግብ ጠባቂው አድኖበታል ።
56ኛው ደቂቃ ላይ በወልቂጤ ከተማ በኩል ጫላ ተሺታ ከራዳን የሱፈሰ በረጅም የተሻገረለትን ኳስ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ይዞ ገብቶ ለጌታነህ ከበደ ለማቀበል ያደረገው ሙከራ ኳሱ ለጥቂት በመርዘሙ አጥቂው ጋር ሳይደርስ ቀርቷል ። በዚህም ጌታነህ ከበደ በጫላ ተሺታ ላይ ብስጭቱን ሲገልፅ ተስተውሏል ።
ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ጫላ ተመሳሳይ ኳስ አግኝቶ ለጌታነህ ለማቀበል ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል ።
61ኛ ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ዳግም ንጉሴን እና ዋሁብን አልፎ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ዊልያም ሰለሞን ሳይደርስበት ቀርቷል ።
ቡናማውቹ ምንም እንኳን ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መውሰድ ቢችሉም ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ደቂቃዎችን መጠበቅ የግድ ብሏቸው ነበር ።
ጨዋታው እስከ 77ኛው ደቂቃ ድረስ በወልቂጤ ከተማ የ3 – 1 መሪነት ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም በቀጣዮቹ 12 ደቂቃዎች ውሰጥ የተቆጠሩ ግቦች የጨዋታውን ውጤት ባልተጠበቀ ሁኔታ ቀይረውታል ።
78ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሀንስ ለአቡበከር ናስር ያቀበለውን ኳስ አቡበከር በግራ የሳጥኑ አቅጣጫ ነፃ ለነበረው ያብቃል ፈረጃ አቀብሎት ያብቃል በግራ እግሩ ወደ ግብ በመምታት የኢትዮጵያ ቡናን ሁለተኛ ግብ አስቆጠሯል ። በሰከንዶች ልዩነች ውሰጥ አቡበከር ናስር ከታፈሰ ሰለሞን የደረሰውን ኳስ በግራ አቅጣጫ እየገፋ ሄዶ ወደ ሳጥን በመግባት ወደ ግብ የመታው ኳስ በሮበርት ኦዶንግካራ መረብ ላይ አርፎ የጨዋታውን ውጤት ወደ 3 – 3 ቀይሮታል ። ግቡም አቡበከር ናስር ከጌታነህ ከበደ ጋር በእኩል በ11 ግቦች የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ደረጃን መምራት አስችሎታል ።
ከመመራት ወደ አቻ መምጣታቸው ያነቃቃቸው የመሰሉት ቡናማዎቹ 89ኛ ደቂቃ ላይ አራተኛ እና የማሸነፍያ ግብ አስቆጥረዋል ። ከያብቃል ግብ ጋር ተመሳሳይነት ባለው መልኩ አቡበከር ናስር ከአማኑኤል ዮሐንስ የደረሰውን ኳስ ለአስራት ቱንጆ አቀብሎት አስራት ቱንጆ በወልቂጤ ከተማ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡናማዎቹ ከጨዋታው ሙሉ ሶሰት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችሏል ።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን ወደ 34 ከፍ ሲያደርግ ደረጃው ግን በነበረበት 6ኛ የሚቀጥል ሲሆን ወልቂጤ ከተማ ደግሞ በነበረበት 29 ነጥብ እና 8ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ24ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 8 ( ሰኞ ) ረፋድ 4:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ሀድያ ሆሳዕናን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 11 ( ረቡዕ ) ረፋድ በተመሳሳይ ረፋድ 4:00 ወልቂጤ ከተማ ከሰበታ ከተማ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናሎ ።