በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቶ ሳይሸናነፉ በአንድ አቻ ውጤት ተለያይተዋል ።
በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ አዲስ አበባ ከተማ በ26ኛው ሳምንት ተጋጣሚዎቻቸውን ሲያሸንፉ የተጠቀሙትን የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ምንም ለወጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
በዝናብ ታጅቦ በተደረገው የ27ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደተለመደው ከኋላ መስርተው በመውጣት ወደ ፊት ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩልም ቡናማዎቹ በተመቻቸ ሁኔታ ኳሱን ይዘው ከሜዳ ክፍላቸው እንዳይወጡ በማድረግ እና እግራቸው ስር የሚገቡ ኳሶችን በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለማድረስ ሲጥሩ ተስተውሏል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ በሁለተኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከአማኑኤል ዮሀንስ በደረሰው ኳስ ቡናማዎቹን ገና በጊዜ ቀዳሚ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ ወደ ግብነት ሳይቀር ቀርቷል ።
- ማሰታውቂያ -
11ኛው ደቂቃ ላይ ያብቃል ፈረጃ ለአበበ ጥላሁን ወደ ኋላ ኳስ ለማቀበል በሚጥርበት ጊዜ ፍፁም ጥላሁን ኳሱን በማግኘት ለሪችሞንድ አቀብሎት የነበረ ሲሆን ሪችሞንድ በቀጥታ የመታው ኳስ ግን ኢላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በጨዋታው 14ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ ወንድሜነህ ደረጄ ባጋጠመው ጉዳት ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ ገዛኸኝ ደሳለኝ ተክቶት ገብቷል ።
ወደ ተጋጣሚ አደገኛ ቀጠና በመድረስ የተሻሉ የነበሩት የመዲናዋ ክለብ ተጫዋቾች ለግብ የቀረቡ ጠንካራ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ።በ17ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ግርማ ከግራ መስመር የተገኘ የቅጣት ምትን ወደ ግብ ክልል አሻግሮ እዮብ በቀታ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግቡ ቋሚ ተመልሷል ።
ከውሀ እረፍት መልስም ጥቃት መሰንዘራቸውን አጠናክረው በመቀጠል በ28ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ጠንካራ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር ። ፍፁም ጥላሁን ከሙሉቀን አዲሱ በረጅም የደረሰውን ኳስ ደረቱ ላይ አብርዶ በግራ እግሩ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሷል ።
ቡናማዎቹ ወደ ፊት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን በአማኑኤል ተስፋዬ እና ታፈሰ ሰለሞን ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው የግብ ሙከራቸውን ሳይሳኩ ቀርተዋል ። የቡድኑ ዋነኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ናስርም የግል ጥረቱን በመጠቀም የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ቢጥሩም የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋቾች ይህ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥረቶችን አድርገዋል ።
በ35ኛው ደቂቃ ግን ጨዋታው ግብ አግኝቷል ። ፍፁም ጥላሁን ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ እንዳለ ከበደ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር አዲስ አበባ ከተማን መሪ አድርጓል ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በመዲናዋ ክለብ መሪነት ተጠናቀቀ ።ሁለተኛውን አጋማሽ ቡናማዎቹ በጥሩ ሁኔታ የጀመሩት ሲሆን በ49ኛው ደቂቃ ላይም ግብ አስቆጥው አቻ መሆን ችለዋል ። አቡበከር ናስር በሳጥን ውስጥ ኳስ ይዞ ልመንህ ታደሰን ለማለፍ በሚጥርበት ጊዜ ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የዕለቱ የመሀል ዳኛ ቴዎድርስ ምትክ የፍፁም ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን አቡበከር ናስርም አስቆጥሮት ከይገዙ ቦጋለ እኩል 14ኛ የውድድር አመቱ የግብ መጠኑ ላይ ደርሷል ።
በአጋማሹ በሁለቱም በኩል ከጨዋታው ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረቶች የነበሩ ሲሆን በሁለቱም በኩል ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ለመመልከት ችለናል ።
በ50 እና በ52ኛ ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ አዶንጎ እና ፍፁም ጥላሁን ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል ። በ53ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ፍፁም ጥላሁን ከግራ መስመር ተነስቶ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ሲመልሰው በቅርብ የነበረው ሪችሞንድ አዶንጎ በድጋሚ ወደ ግብ ሞክሮ በረከት አማረ በድጋሚ መልሶታል ።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል በሁለቱ መስመሮች ላይ ባሉት አላዛር ሽመልስ እና ዊልያም ሰለሞን አማካኝነት አቡበከር ናስርን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር ።
በ55ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ሰለሞን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አብነት ደምሴ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ቡናማዎቹ ይበልጥ ኳሱን በመቆጣጠር ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
69ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከታፈሰ ሰለሞን በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ ለማስቆጠር ሲሞክር ዳንኤል ተሾመ ወጥቶ መልሶበታል ። ከዚህም በተጨማሪ አቡበከር ከአማኑኤል ዮሀንስ እና አላዛር ሽመልስ ተመሳሳይ ኳሶችን ማግኘት ቢላኩለተም ኳሶቹ ላይ መድረስ ሳየችል ቀርቷል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች በተለይም ተቀይሮ ለገባው መሀመድ አበራ በሚደርሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረው ነበር ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ ጥሩ ዕድል ለማግኘት ቢችሉም አቡበከር ናስር ኳሱን ለመጠቀም በሚጥርበት ጊዜ ሮቤል ግርማ ተንሸራቶ ኳሱን አስጥሎታል ። በመጨረሻም ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ41 ነጥብ በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ሲገደድ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በ29 ነጥብ ድሬዳዋ ከተማን በግብ ክፍያ በልጦ ከወራጅ ቀጠና በመውጣት 13ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ችሏል ።
በ28ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 16 ( ሐሙስ ) 10:00 ላይ አዲስ አበባ ከተማ ሰበታ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ረፋድ 4:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከአርባ ምንጭ ከተማ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ።