በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከፋሲል ከነማ አገናኝቶ በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች ጨዋታው አንድ ለአንድ ተጠናቋል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በ13ኛው ሳምንት በአርባ ምንጭ ከተማ በተሸነፉበት ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በቴዎድሮስ በቀለ ፣ ዊልያም ሰለሞን እና እንዳለ ደባልቄ ምትክ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል እና አቡበከር ናስር የተሰለፉ ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩልም በሳምንቱ በሀዋሳ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው አሰላለፍ በተመሳሳይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ አምሳሉ ጥላሁንን ፣ በዛብህ መለዮን እና ፍቃዱ አለሙን በአስቻለው ታመነ ፣ ሳሙኤል ዮሀንስ እና ኦኪኪ አፎላቢ ምትክ በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ያስመለከተ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ካለፈው ጨዋታ በተሻለ ኳሱን ከኋላ መስርተው ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶችን ያደረጉበት ሲሆን በተለይም የፊት አጥቂውን አቡበከር ናስርን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች ወደ ፊት ሲደርሱ ነበር ። በፋሲል ከነማ በኩል ኳሶችን በቶሎ ወደ ፊት በመውሰድ እና ከፊት መስመር ባሉ ተጫዋቾች ጫና ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያው የነበረው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 12ኛ ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ የተደረገ ሲሆን በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በአቤል ማሞ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
መሀል ላይ የነበሩ እንቅስቃሴዎች በርከት ያሉበት ይህ የጨዋታ አጋማሽ በግብ ሙከራዎች ረገድ ቀዝቀዝ ብሎ የቆየ ሲሆን በ36ኛው ደቂቃ ላይ ግን የመጀመሪያውን ግብ አስመልክቶናል ። ቡናማዎቹ ከኋላ መስርተው ለመውጣት በሚያደርጉች ጥረት ኳሱን መንጠቅ የቻሉት አፄዎቹ በበረከት ደስታ ለጎል አመቻቺነት እንዲሁም በበዛብህ መለዮ አስቆጣሪነት ቀዳሚ መሆን ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በተወሰነ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ወደ ፊት ለመሄድ ችለው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሱራፌል ዳኛቸው በታፈሰ ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት የቅጣት ምች ማግኘት ችለዋል ። የቅጣት ምቱንም ጎል አዳኙ አቡበከር ናስር ወደ ግብ ሞክሮት የግቡ ቋሚ ሲመልሰው ኳሱን ያገኘው አበበ ጥላሁን 44ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ ቡናማዎቹን አቻ አድርጓል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች መስርተው ለመውጣት በሚጥሩበት ጊዜ በድጋሚ የተነጠቁ ሲሆን ኳሱን ያገኘው ሱራፌል ዳኛቸው አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛው የጨዋታ ብልጫ በአፄዎቹ ስር የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። ቡናማዎቹ በተፈጠረባቸው ጫና ወደ ኋላ ለማፈግፈግ የተገደዱ ሲሆን የሚነጠቁ ኳሶችን ግን በፈጣን ወደ ፊት ለመላክ ጥረቶችን ቢያደርጉም አብዛኞቹ ኳሶች የፋሲል ከተማ ተከላካዮችን ማለፍ አልቻሉም ።
58ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ አከታትሎ ወደ ግብ የላካቸው ኳሶች በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ዕድሎች የነበሩ ሲሆን በቅድሚያ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በአቤል ማሞ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የማዕዘን ምቱም በሱራፌል ዳኛቸው ሲሻገር የደረሰው በረከት በግንባር ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በአስራት ቱንጆ ተመልሷል ።
በአጋማሹ አብዛኛው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ቡና ሳጥን አካባቢ የነበረ ሲሆን አፄዎቹ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ግን ፍሬያማ መሆን አልቻሉም ። በረከት ከሞከራቸው ኳሶች ሌላ ሊጠቀስ የሚችለው የግብ ሙከራ 82ኛ ደቂቃ የተደረገ ነበር ። ግብ አስቆጣሪው በዛብህ መለዮ ከያሬድ ባየህ በረጅም የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ጠንከር አድርጎ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም በአቤል ማሞ ሊድንበት ችሏል ። ከዚህ ሙከራ ሰከንዶች በኋላ በፋሲል ከተማ በኩል ከመሰመር የተሻገረለትን ኳስ ሽመክት ጉግሳ እግሩን በከፍታ አንስቶ ለማግኘት ሲሞክር የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ላይ ከባድ ጥፋት የሰራ ቢሆንም ዳኛው በዝምታ ያለፉት ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ቅሬታቸውን ሜዳ ላይ ገልፀዋል ።
በሁለቱም በኩል ሶስት ነጥቡን ለማግኘት የተለያዩ ቅያሪዎችን ማድረግ ቢችሉም በድጋሚ ኳስ እና መረብን የሚያገናኝ ተጫዋች ሳያገኙ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 19 ቢያደርስም ደረጃውን ማሻሻል ሳይችል በነበረበት 7ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ሲገደድ ፋሲል ከነማ በበኩሉ ነጥቡን 23 በማድረስ ሀዋሳ ከተማን በግብ ክፍያ በልጦ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።
በ15ኛው ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን ፋሲል ከተማ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።