የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠኝ ሳምንታት ጨዋታዎችን በሀዋሳ ከተማ አካሂዶ ለአፍሪካ ዋንጫ ከተቋረጠ በኋላ በዛሬው ዕለት በድሬዳዋ ከተማ ወደ ውድድር ተመልሷል ።
የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከሀዋሳ ከተማ ያገናኘ ሲሆን ሀይቆቹ ከእረፍት መልስ በብሩክ በየነ እና በመስፍን ታፈሰ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
ኢትዮጵያ ቡና በዘጠነኛ ሳመንች በሀድያ ሆሳዕና በተሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ወደ ደቡብ አፍሪካ በተጓዘው አቡበከር ናስር እና ሮቤል ተክለሚካኤል ቦታ እንዳለ ደባልቄን እና ታፈሰ ሰለሞንን ይዘው ገብተዋል ። በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ አርባምንጭ ከተማን ካሸነፉበት ጨዋታ በዮሀንስ ሰጌቦ እና ወንድማገኝ ማዕረግ ቦታ መድኃኔ ታደሰን እና አብዱልባሲጥ ከማልን ጨዋታውን እንዲጀምሩ አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮጵያ ቡና በ4-3-3 አሰላለፍ ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን ኳሱን ከኋላ መስመርተው በመውጣት ለማጥቃት ፍላጎለቶች የነበሩ ቢሆንም ሀዋሳ ከተማዎች በመሀል ክፍሉ ላይ የቁጥር ብልጫን በመውሰድ ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀላሉ ከራሳቸውን የሜዳ ክልል እንዳይወጡ ማድረግ ችለው ነበር ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በመሀል ላይ በመብዛት የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል በመሄድ በተለይም በብሩክ በየነ በመስፍን ታፈሰ በሚመራው የፊት መስመር በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል ።
በ4ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከብሩክ በየነ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በአቤል ማሞ ተመልሶበታል ። በ18ኛው ደቂቃ ላይም በተመሳሳይ መስፍን ከብሩክ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ለመሞከር ያደረገው ጥረት ኳሱ ከግቡ አናት በላይ በመሄዱ ሳይሳ ቀርቷል ከአራት ደቂቃዎች በኋላ መስፍን ከተከላካዮች ጀርባ አምልጦ በመግባት ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ይዞ ለመሄድ ሲሞክር ኳሱ ረዝሞበት በግብ ጠባቂው ሊያዝበት ችሏል ።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል በአጋማሹ ለግብ የቀረበ ሙከራ በ10ኛው ደቂቃ ያደረጉ ሲሆን አቤል እንዳለ ከዊልያም ሰለሞን ያገኘውን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ወደ ግብ ሞክሮት ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ። በፈጣን ሽግግሮች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ31ኛ ደቂቃ ላይ በብሩክ በየነ አማካኝነት ያገኙተን ኳስ ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል ። ከዚህ አጋጣሚ ሶስት ያህል ደቂቃዎች በፊት በቃሉ ገነነ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል ቀርቷል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለምንም ግብ ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ገና ሶስት ያህል ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ቴዎድሮስ በቀለ በሳጥን ውስጥ ወንድማገኝ ሀይሉ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማዎች የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ብሩክ በየነ ግብ ጠባቂው በወደቀበት ተቃራኒ መቶ አስቆጠረ ።
በአጋማሹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይም በቀኝ መስመር ላይ አድልተው ለማጥቃት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች በአቅጣጫው ወደ ሳጥን ለመግባት ሙከራዎች አድርገዋል ። በሀዋሳ ከተማ በኩል በረጃጅም ኳሶቾ እና በፈጣን ሽግግር የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች የሚፈጥሩትን ክፍተቶች ተጠቅመው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።
በ55ኛ ደቂቃ ላይ በቃሉ ገነነ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ አዲስአለም ተስፋዬ ጋር ደርሶ ወደ ግብ የተመታው ኳስ በአበበ ጥላሁን ለጥቂት ከግቡ መስመር ላይ ተመልሷል ። ከአምሰት ደቂቃዎች በኋላ ኤፍሬም አሻም በረጅም የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ክልል አሻግሮ ብሩክ በየነ ቢያገኘውም በአበበ ጥላሁን ተጨርፎ በአቤል ማሞ ተመልሷል ።
62ኛ ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከአብዱልባሲጥ ከማል በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች መሀል አልፎ የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በግሩም አጨራረስ የሀዋሳ ከተምን ሁለተኛ ግብ አስቆጠረ ።
በሁለት ግብ ልዩነት የተመሩት ቡናማዎቹ በ69ኛ እና በ73ኛ ደቂቃ ላይ በስዩም ተስፋዬ እና በታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም ኳስ ከመረብ ማገናኘት አልቻሉም ። ግብ በመፈለግ ላይ የነበሩት ቡናማዎቹ የተጫዋች ቅያሪ ለማድረግ 89 ያህል ደቂቃዎችን ጠብቀው ነበር ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል የኢትዮጵያ ቡናን የተከላካይ ክፍል ክፍትት በመጠቀም በ84ኛ ደቂቃ ላይ በተባረክ ሄፋሞ አማካይነት ገዘጥሩ ግብ መሆን የሚችል ዕድልን ቢፈጥሩም ወደ ግብ የተሞከረው ኳስ ኢላማውን መጠበቅ ሳየችል ቀርቷል ። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ አራት ያህል ደቂቃዎች ከተጨመሩ በኋላ የጨዋታው መጠናቀቂያ ጊዜ 8 ያህል ሰከንዶች እየቀሩት የዕለቱ የመሀል ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ በፊሽካቸው ድምፅ አሳወቁ ።
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎም ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 17 በማድረስ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ኢትዮጵያ ቡና በ14 ነጥብ በነበረበት የስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።