በሊጉ የሶስተኛ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስመለክተን ተጠናቋል ።
ምሽት 12:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች በደጋፊዎቻቸው ታጅበው ጨዋታቸውን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሱን ከኋላ መስርተው ለመውጣት በተደጋጋሚ ሲያደርጉት የነበረው ሙከራ በሲዳማ ቡና ተጨዋቾች ሲመክን ነበር ።
አልፎ አልፎም በረጅም ከፊት መስመር የሚጣሉ ኳሶች ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች ሲሳይ ሆነዋል ። በሲዳማ ቡና በኩል ተጋጣሚ ኳስን መስርቶ ለመውጣት ሲሞክር ኳሱን በመንጠቅ ከፊት መስመር ባሉ አጥቂዎቻቸው አማካይነት ጫና በማድረግ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በፍሬው ሰለሞን በብሩክ ሙሉጌታ እና በሰለሞን ሀብቴ የተደረጉት ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው ።
- ማሰታውቂያ -
በኢትዮጵያ ቡና በተለይም በቆሙ ኳሶች ላይ የነበረባቸው ድክመት ግብ እንዲቆጠርባቸው ሊያደርግ ይችል ነበር ። በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያ አጋማሽ የነበራቸውን ጫና በማስቀጠል በተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና መፍጠር ቢችሉም ቴዎድሮስ ታፈሰ 54ኛ ደቂቃ ላይ ከርቀት አክርሮ ከመታው ኳስ ውጪ ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ከ70 ደቂቃ በኋላ ተረጋግተው ወደ ፊት በመሄድ በተጋጣሚያቸው ላይ ከቀደሙት ደቂቃዎች በተሻለ ጫና የፈጠሩ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ዊልያም ሰለሞንን ቀይሮ የገባው ሮቤል ተክለሚካኤል በ72 እና 81ኛ ደቂቃዎች ላይ ከርቀት ወደ ግብ የመታቸው እና በግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ የተመለሱት ኳሶች አስደናቂ ነበሩ ።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ የተገደዱት ሲዳማ ቡናዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ለመሄድ ቢሞክሩም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም ። በስተመጨረሻም የሁለቱ ቡናዎች ጨዋታ ያለ ምንም ግብ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።