በ17ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው የኢትዮጵያ ትልቁ ደርቢ ሸገር ደርቢ በቅዲስ ጊዮርጊስ የ4 ለ 0 አሸናፊነት ተፈፅሟል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በ16ኛው ሳምንት ከሲዳማ ቡና አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ስድስት ለውጦችን አድርገው የገቡ ሲሆን ስዩም ተስፋዬ ፣ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ተመስገን ገብረኪዳንን በሀይሌ ገብረትንሣይ ፣ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ ዊልያም ሰለሞን ፣ አቤል እንዳለ እና እንዳለ ደባልቄ ምትክ ሲያስገቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በሳምንቱ ሰበታ ከተማን ሲረቱ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ቻርለስ ሉክዋጎን እና ሱሌማን ሀሚድን በባህሩ ነጋሽ እና ያሬድ ሀሰን ምትክ አሰልፈዋል ።የጨዋታው ጊዜ ገና በሰከንዶች እድሜ ሳለ ግብ ሊያስተናግድ የነበረ ሲሆን የፍሪምፖንግን ሰህተት ተከትሎ አቡበከር ናስር የግብ ጠባቂውን መውጣት በመመልከት ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ። ኢትዮጵያ ቡናዎች በሌሎች ጨዋታዎቻቸው ላይ ስንመለከት እእንደነረው ከኋላ መስርተው ለመውጣት የሞከሩ ሲሆን በቀላሉ ለመውጣት ተቸግረው በሚቀሟቸው ኳሶች አደጋ ያላቸውን ኳሶች ሲያስተናግዱ ነበር ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጫን ብለው በመጫወት የኢትዮጵያ ቡናን ምስረታ ለመግታት ጥረቶችን ያደረጉ ቢሆንም ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ግን በቀላሉ ለመጠቀም ተስኗቸው ነበር ። በ5ኛው ደቂቃ ላይ ያብስራ ተስፋዬ ከስዩም ተስፋዬ የነጠቀውን ኳስ ወደ ግብ ቀየረው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ውጪ የመታው ኳስ አንዱ ማሳያ ነበር ።
በ11ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ምኞት በግንባር መግጨት ቢችልም ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ በቀላሉ ይዞታል ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አቡበከር ናስርን ኢላማ ያደረጉ ኳሶች ወደ ፊት ለማድረስ በመሀል ክፍል ተጫዋቾች አማካኝነት ጥረቶች ሲደረጉ የነበረ ቢሆንም የምኞት እና የፍሪምፖንግ ጥምረት ይህን ከማድረግ አግዷቸዋል ።
- ማሰታውቂያ -
የቡናማዎቹ ከኋላ የመመስረት እና የፈረሰኞቹ ጫና መፍጠር በ14ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ የታየ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ ላይ ስዩም ተስፋዬ ለገዛኸኝ ደሳለኝ ለማድረስ የሞከረው ኳስ በአቤል ያለው እግር ስር ገብቶ የነበረ ቢሆንም ገዛኸኝ ተንሸራቶ ኳሱን በማውጣት አቤልን ግብ ከማስቆጠር ሊያግደው ችሏል ።
ፈረሰኞቹ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ከቀኝ መስመር በኩል በተለይም በሱሌማን ሀሚድ አማካኝነት በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራዎችን አድርገው ነበር ። በዚሁ አቅጣጫ 33ኛ ደቂቃ ላይ ያብስራ ተስፋዬ ለሀይደር አቀብሎት ሀይደር ወደ ግብ የላከው ኳስ በአቤል ማሞ እጆች ላይ አርፏል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቡናማዎቹ የተከላካይ መስመር ላይ የፈጠሩትን ጫና ማስቀጠል ቢችሉም የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙ ደቂቃዎች የሄዱ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ ወደ ፈረሰኞቹ የግብ ክልል መቅረብ ዳገት ሆኖባቸው ነበር ።
በ41ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሱሌማን ሀሚድ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ኳሱ ላይ ባለመድረሱ ሳይሳካ ቀርቷል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ግን የጨዋታ ቀዳሚ እና ፈረሰኞቹን መሪ ያደረገ ግብ ተቆጥሯል ።ቸርነት ጉግሳ በቀኝ መስመር በኩል አስራት ቱንጆን እና አማኑኤል ዮሀንስን በማታለል ለአማኑኤል ገብረሚካኤል ያደረሰው ሲሆን አማኑኤልም ኳሱን አረጋግቶ ለአቤል ያቀበለው ሲሆን ጀርባውን ለግብ ሰጥቶ ኳሱን የተቀበለው አቤል ያለውም ኳሱን እነደያዘ ዞሮ በመምታት በሞክሼው መረብ ላይ አሳርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ምኞት ደበበ በአቡበከር ናስር ላይ ከባድ የሚመስል ጥፋት ሰርቶበት የነበረ ቢሆንም በወደቀበት ከባድ የህመም ስሜት ላይ የነበረው ኡበበከር ከተሰጠው ህክምና በኋላ ተነስቶ ጨዋታውን መቀጠል ችሏል ።የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ የፈረሰኞቹን መሪነት ወደ 2 ከፍ ያደረገ ግብ አስቆጠሯል ። አበበ ጥላሁን በሚገባ መቆጣጠር የተሳነው ኳስ በያብስራ እገር ስር ከገባ በኋላ በሀይደር ሸረፋ በኩል ለቸርነት ጉግሳ ደርሶ ቸርነት የግብ ጠባቂውን የአቤል ማሞን መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ ከመረብ ላይ አርፏል ።
በአጋማሹ ቡናማዎቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳሱን መስርተው መውጣት እና ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ማለፍ ቢችሉም በውድድር አመቱ በ16 ጨዋታዎች ላይ 7 ግቦችን ብቻ ያስተናገደውን የፈረሰኞቹን የተከላካይ መስመር አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረዋል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሚነጠቁ ኳሶችን በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ እና የግብ ክልል በማድረስ ተጨማሪ ግቦችን ለማከል ሲታትሩ ነበር ።
በ49ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው 7 ቁጥር ለባሽ ሚክያስ መኮንን በምኞት ደበበ ላይ ከባድ እና ኳስ ከማስጣል ያለፈ ጥፋት ሰርቶ የነበረ ቢሆንም የዕለቱ የመሀል ዳኛ በማስጠንቀቂያ የቢጫ ካርድ ያለፉት ሲሆን አሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ ግን ወድያውኑ በሀይሌ ገብረትንሳይ ቀይሮ አስወጥቶታል ።በ76ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ኡበበከር ናስር ለማግኘት ቢጥርም ኳሱ ላይ መድረስ ሳይችል ቀርቷል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከጉዳት መልስ በተሰለፋባቸው ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር የቻለው እና በጨዋታውም አቤል ያለውን ቀይሮ የገባው አዲስ ግደይ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ከአማኑኤል ገብረሚካኤል ግሩም ኳስ ደርሶት የነበረ ቢሆንም በዕለቱ በቡናማዎቹ በኩል በአንፃራዊነት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነረበው ገዛኸኝ ደሳለኝ ደርሶ አውጥቶበታል ።
በ82ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ ያገኙትን የማዕዘን ምት በሄኖክ አዱኛ ሲሻገር ሌላኛው ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባር በመግጨት የቢጫ እና ቀይ ለባሾቹን መሪነት ወደ 3 ለ 0 ከፍ አድርጓል ። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም አዲስ ግደይ ሀይሌ ገብረትንሳይ በሳጥኑ ቅርብ ርቀት ላይ በሰራበት ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ መቶ በማራኪ ሁኔታ ግብ አድርጎታል ። ይህም ተጫዋቹ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች ላይ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች ሶሰት እንዲያደርስ አስችሎታል ።በመጨረሻም ጨዋታው በፈረሰኞቹ የ4 ለ 0 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።የጨዋታው ውጤት ፈረሰኞቹ ነጥባቸው 37 በማድረስ መሪነታቸውን እንዲያጠናክሩ ሲያደርግ ቡናማዎቹን ደግሞ ከነበሩበት 8ኛ ደረጃ ወደ 9ኛ ደረጃ አንሸራቷቸዋል ።
በ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና በመጪው ማክሰኞ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሰበታ ከተማን ሲገጥም ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ሰዓት ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳል ።