በኢትዮጵያ ቡና እና መከላከያ መካከል የተደረገው ጨዋታ ለረጅም ደቂቃዎች ሲመሩ የነበሩት ቡናማዎቹ ነጥብ ለመጋራት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ ደቂቃ የተሰጠባቸውን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት አማረ መልሶት ቡናማዎቹ 1 ለ 0 አሸንፈው ወጥተዋል።
ኢትዮጵያ ቡና በአምስተኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ባሸነፈበት ጨዋታ የተጠቀመውን ምርጥ 11 በድጋሚ የተጠቀመ ሲሆን መከላከያ በበኩሉ ባህርዳርን ባሸነፈበት ጨዋታ ከተጠቀመው ምርጥ 11 ቢንያም ላንቃሞን እና አለምአንተ ካሳን ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው ጅማሮ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ በመንቀሳቀስ ቢጀምሩም ቀስ በቀስ መከላከያዎች ወደ ጨዋታው በመመለስ ተመጣጣኝ የሆነ ጨዋታ አስመልክተውናል ።
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታውን በመቆጣጠር ወደ ፊት በመጓዝ ጫና ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉት ቡናማዎቹ የመከላከያን የተከላካይ መስመር ከባድ ሆኖባቸው ነበር ። በ12ኛ ደቂቃ ላይ ሀይሌ ገብረትንሳይ ለአቡበከር ናስር በአየር ላይ የላከለትን ኳስ አቡበከር በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ቢሞክርም በክሌመንት ቦኔ ተይዞበታል ። የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደባቸው መከላከያዎች የሚነጥቋቸውን ኳሶቾ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ክልል በመውሰድ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። 19ኛ ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ከሳጥን ውጨ የሞከረው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
ቀስ በቀስ ብልጫ እየወሰዱ የመጡት መከላከያዎች ይህ ነው ሊባል የሚችል የግብ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው ነበር ። ከውሀ እረፍት በኋላ ቡናማዎቹ ቀደም ብሎ ከነበረው በተሻለ በመንቀሳቀስ የመከላከያነሰ የተከላካይ ክፍል መፈተን ችለዋል ።
39ኛ ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከኋላ ጀምሮ በጥሩ ቅብብል የሄደው ኳስ በሮቤል ተክለሚካኤል አቀባይነት በዊልያም ሰለሞን ጨራሽነት ቡናማዎቹ ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ግብ አስቆጠሩ ።
ከግቧ በኋላ በ41ኛ ደቂቃ ላይ መከላከያዎቾ ከሳጥኑ ውጪ በቀኝ በኩል ያገኙትን የቅጣት ምች ቢንያም በላይ ወደ ግብ መቶት የግቡ ቋሚ መልሶበታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በኢትዮጵያ ቡና መሪነት ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ በአብዛኛው ቀዝቃዛ የነበረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስመለከት ነበር ። ነገር ግን በተለይም እነተመሩ የነበሩት መከላከያዎች በተሻለ ለመንመቀሳቀስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ግብ ማግኘት ግን ከብዷቸው ቆይቷል ። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመሄድ ቢሞክሩም በሁለተኛው አጋማሽ አብዛኛው የጨዎታ ቁጥጥር በተጋጣሚያቸው ስር ነበር ።
57ኛ ደቂቃ ላይ አቡበከር ናስር ከሮቤል ተክለሚካኤል በረጅም የተጣለለትን ኳስ በሳጥን ውስጥ ሆኖ አግኝቶ በጠንካራ ምት ወደ ግብ ቢሞክረውም ክሌመንት ቦዬ ኳሱን የማዕዘን ምት አድርጎታል ። በመከላከያ የበላይነት አልፎ አልፎ ደግሞ የቡናማዎቹ ማጥቃት በተወሰነ መልኩ የታየተበት ጨዋታ እስከ 80ኛ ደቂቃ ድረስ ለአይን ሳቢ ያልነበረ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ነበር ። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች መከላከያዎች በከፍተኛ ጫና መጫወት የቻሉበት ነበር ።
በዚህም 88ኛ ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ሀይሉ በረጅም የተላከለትን ኳስ ለማግኘት ሲሞክር የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ ጥፋት ሰርቶበት መከላከያዎች የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። ጥፋቱን የሰራው አቤል ማሞ በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ። በምትኩ ተቀይሮ የገባው በረከት አማረ በቢንያም በላይ የተመታውን የፍፁም ቅጣት ምት አድኖ ቡናማዎቹን ሶሰት ነጥብ ይዘው እንዲወጡ አስችሏል ።
የጨዋታውን ውጤት ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 8 ሲያደርስ መከላከያ በበኩሉ 10 ነጥብ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።