በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከተማ ሰበታ ከተማን 3 ለ 0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ መሪው የተጠጋበትን ድል አስመዝግቧል ።
ፋሲል ከተማ በ10ኛ ሳምንት ጨዋታ በቅዱሰ ጊዮርጊስ በሰፊ ውጤት በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ያህል ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን ሰይድ ሀሰን ፣ ከድር ኩሊባሊ እና ሀብታሙ ተከስተ ፤ አለምብርሀን ይግዛውን ፣ ያሬድ ባየህን እና በዛብህ መለዮን ተከትው ሲገቡ በሰበታ ከተማ በኩልም በአዳማ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን አንተነህ ናደውን ፣ በኃይሉ ግርማን እና አክሊሉ ዋለልኝን በአለማየሁ ሙለታ ፣ በበረከት ሳሙኤል እና አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
በጨዋታው ፋሲል ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ መጫወት የቻሉ ሲሆን በግብ ዕድሎችም የተሻሉ ነበሩ ። በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች ወደ ፊት በሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች ጥሩ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በመከላከሉ ደግሞ የፋሲልን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ በተለየም በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ለመንቀሳቀስ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
2ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ ተጨርፎ በግብ ጠባቂው በቀላሉ ተይዟል የተያዘ ሲሆን 20ኛው ደቂቃ ላይ በሰበታ ከተማ በኩል ዘካርያስ ፍቅሬ ከሳሙኤል ሳሊሶ በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ አግኝቶት ከግቡ ለቆ የወጣውን ሚካኤል ሳማኪን ማለፍ ቢችልም ከድር ኩሊባሊ በፍጥነት ደርሶ ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶበታል ።
በጥሩ የፉክክር መንፈስ የቀጠለው ጨዋታ በተሳኩ የግብ ሙከራዎች ባይታገዝም በሁለቱም በኩል ግብ ለማግኘት የሚደረጉት ጥረቶች በተደጋጋሚ ይታዩ ነበር ። በሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ሌላ በበረከት ሳሙኤል እና ኦኪኪ አፎላቢ የነበረው ሽኩቻ ትኩረት የሳበ ነበር ።
42ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ምርጥ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በለአለም ብርሀኑ ለጥቂት ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ 45ኛ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ በረከት ደስታ በጭንቅላት ገጭቶ ግብ አድርጎታል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበረው በተሻለ በግብ ሙከራዎች እና ፈጣን እንቅስቃሴዎች የታጀበ ነበር ። በመመራት ላይ የነበሩት ሰበታ ከተማዎች ወደ ፊት በመሄድ የተሻሉ በመሆን አጋማሹን መጀመር ቢችሉም በሶስተኛው የማጥቃት ዞን ሲገቡ የነበረባቸው ክፍተቶች እና የፋሲል ከተማ ተከላካዮች ንቁ ሆኖ መጫወት የግብ ሙከራዎችን በቀላሉ ማድረግ እንዳይችሉ አድርጎቸዋል ። በፋሲል ከተማ በኩል በረጃጅም እና በፈጣን ሽግግሮች በመጫወት ለማጥቃት ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል ።
63ኛ ደቂቃ ላይ በአምሳሉ ጥላሁን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ሞክሮት የግቡ ቋሚ የመለሰውን ኳስ ሰይድ ሀሰን ወዲያውኑ አግኝቶ በማስቆጠር የፋሲል ከተማን መሪነት ወደ 2 ለ 0 ከፍ አደረገ ።
ከግቡ በኋላ ፋሲል ከተማዎች በተሻለ መነቃቃት ሲጫወቱ በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች የነበራቸው የማጥቃት አጨዋወት በተወሰነ መልኩ ተቀዛቅዞ ነበር ።
74ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከመስመር ተነስቶ ይዞት የሄደውን ኳስ ለሽመክት ጉግሳ በጥሩ ሁኔታ ቢያቀብለውም ሽመክት ወደ ግብ የመታው ኳስ በለአለም ብርሀኑ ተመልሷል ። የጨዋታው የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል የደረሱባቸው ሳቢ የጨዋታው ጊዜያት ነበሩ ።
81ኛ ደቂቃ ላይ በሳጥን ውሰጥ ሽመክት ጉግሳ ላይ በተሰራ ጥፋት አፄዎቹ ያገኙትን የቅጣት ምት ኦኪኪ አፎላቢ ቢመታውም ኳሱ የግቡ አግዳሚ ለትሞ ተመልሷል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ኦኪኪ በግራ መስመር የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወቶበታል ።
85ኛ ደቂቃ ላይ በሰበታ ከተማ በኩል ዘካርያስ ፍቅሬ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በሚካኤል ሳማኪ በቀላሉ ነበር የተያዘው ።
86ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከርቀት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በለአለም ብርሀኑ እና በግቡ አግዳሚ ተጨርፎ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የማዕዘን ምቱን ልክ እንደመጀመሪያው ግብ ሱራፌል ዳኛቸው አሻግሮት በበረከት ደስታ ተቆጥሯል ። በስተመጨረሻም አፄዎቹ በሶሰት ግብ ልዩነት በማሸነፍ ባሳለፍነው ሳምንት ከደረሰባቸው ሽንፋት ማገገማቸውን አሳይተዋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ፋሲል ከተማ ነጥቡን 21 በማድረስ 2ኛ ደረጃውን ሲያስጠብቅ ተሸናፊው ሰበታ ከተማ ባለበት 7 ነጥብ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ12ኛ ሳምንት ፋሲል ከተማ አዳማ ከተማን እንዲሁም ሰበታ ከተማ ደግሞ ሀድያ ሆሳዕናን የሚገጥሙ ይሆናል ።