የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ መካከል ተደርጎ በአንድ ለአንድ ውጤት ተጠናቋል ።
ፋሲል ከነማ በ11ኛ ሳምንት ሰበታ ከተማን 3 ለ 0 በረቱበት ጨዋታ የነበረውን ቋሚ አሰላለፍ ምንም ሳይቀይሩ የገቡ ሲሆን በአዳማ ከተማ በኩል ከኢትዮጵያ ቡና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ የሁለት ተጫዋች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ታደለ መንገሻን እና አብዲሳ ጀማልን በዮሴፍ ዮሀንስ እና አሜ መሀመድ ተክተው ገብተዋል ።
ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ አዳማ ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው በአንፃራዊነት ተሽለው የቀረቡበት ነበር ። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይም ምንም እነኳን ኢላማቸውን የጠበቁ ባይሆኑም ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉበት ነበር ። በአዳማ ከተማዎች በኩል በመሀል ላይ በቁጥርም ሆነ ጫና በመፍጠር ተሽለው በመገኘት ከፋሲል ከተማዎች የተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ችለዋል ። በፋሲል ከነማ በኩል በተወሰኑ አጋጣሚዎች በረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ያደረጓቸው ጥረቶች ደካማ ነበሩ ።
- ማሰታውቂያ -
ከውሀ እረፍት መልስ 30ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ በኩል የመጀመሪያው ግብ ተቆጥሯል ። ጀሚል ያዕቆብ ከቀኝ መስመር ላይ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ አሜ መሀመድ ኳሱ አየር ላይ እንዳለ በመምታት አስገራሚ ግብ በማስቆጠር አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል ። በመሀል የሜዳው ክፍል ላይ ያመዘነው የመጀመሪያው አጋማሽ ሌላ ግብም ሆነ ጠንከር ያለ የግብ ሙከራ ሳያስተናግድ በአዳማ ከተማ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ አፄዎቹ ከጅምሩ ተጭነው መጫወት የቻሉበት ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማሻሻል የቀረቡበት ነበር ። በአዳማ ከተማ በኩል በአመዛኙ በመከላከል አጋማሹን የተጫወቱ ሲሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል ለመፈተን ያደረጉት ጥረት ያን ያህል በጥሩ ሊነሳ የሚችል አልነበረም ።
74ኛ ደቂቃ ላይ ከእጅ ውርወራ የተነሳውን ኳስ አለምብርሀን ይግዛው ወደ ግብ አሻግሮት ኦኪኪ አፎላቢ የጀማል ጣሰውን ስህትት ተጠቅሞ አፄዎቹም አቻ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ። ከግቡ መቆጠር በኋላም የፋሲል ከተማ የበላይነት ቀጥሎ የታየበት ነበር ።
86ኛ ደቂቃ ላይ የበረከት ደስታ ኦኪኪ አፎላቢ እና ፍቃዱ አለሙ ግሩም ቅብብል ወደ አዳማ ከተማ ሳጥን ቢደርስም ግብ ጠባቂው ጀማል ወጥቶ መልሶታል ። የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት የመታው እና ከድር ኩሊባሊ ከማዕዘን የተሻገረን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ በጀማል ጣሰው አማካኝነት ግብ ከመሆን ድነዋል ። ጨዋታውም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ክለቦች ነጥባቸውን በአንድ አንድ ነጥብ ማሻሻል ቢችሉም ደረጃቸው ግን ባሉበት የሚቀጥል ይሆናል ።
በ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ ሀዋሳ ከተማን አዳማ ከተማ ደግሞ መከላከያን የሚገጥሙ ይሆናል ።