የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የ2013 የሊጉ ሻምፕዮን ፋሲል ከተማን ከ 2011 ሻምፕዮኑ ጅማ አባ ጅፋር አገናኝቶ ፋሲል ከተማ 4 ለ 0 በማሸነፍ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ ችሏል ።
በጨዋታው በፋሲል ከተማ በኩል በሁለተኛው ሳምንት ወልቂጤን ካሸነፈው ቋሚ 11 ሁለት ቅያሪዎች የነበሩ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ በአዳማ ከተማ ከተሸነፈው ቡድን አራት ያህል ቅያሪዎች ነበሩ ።
ጨዋታው በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን በፋሲል ከተማ በኩል ኳሱን ከራሳቸው ሜዳ በመጀመር ወደ ማጥቃት መሸገጋርን ምርጫቸው አድርገው የተጫወቱ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል በፈጣን መልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ሙከራዎችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ6ኛው ደቂቃ ፍቃዱ አለሙ ከበረከት ደስታ ተሻግሮለት የሞከረው ኳስ እንዲሁም 13ኛ ደቂቃ ላይ በረከትደስታ ከአብዱልከሪም መሀመድ የደረሰውን ኳሶ ዞሮ ወደ ግብ መቶት የሳቷቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው ። በጅማ አባጅፋር በኩል 19ኛው ደቂቃ ላይ ሮጀር ማላ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር ። 32ኛ ደቂቃ ላይ ጨዋታው የመጀመሪያውን ግብ አገኘ ።
በረከት ደስታ ኳሱን እየገፋ በሳጥን ውስጥ በገባበት ጊዜ በአስናቀ ሞገስ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውኖ የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ያሬድ ባየህ አስቆጠረ ። ከዚህ በኋላም በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ጅማ አባ ጅፋሮች ጫና ፈጥረው በመጫወት ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ቢያደርጉም ፈታኝ የሆነ የግብ ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም ነበር ። በፋሲል ከተማ በኩል በተረጋጋ መንፈስ በመጫወት በተለይም በሁለቱ ክንፎች በኩል ጫና ሲፈጥሩ ቆይተዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በፋሲል ከተማ መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ አፄዎቹ ኳሱን ከኋላ መስርተው በመውጣት ተጋጣሚ ወደ ሜዳ ክፍላቸው ሲመጣ ፈጣን ኳሶችን በክንፍ ላሉት በረከት እና ሽመክት በማድረስ ጥሩ ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ያደረጉ ሲሆን በጅማ አባጅፋር በኩል የማጥቃት ዘዴያቸውን ከክንፍ ወደ ግብ አቅራቢያ ላሉ የአጥቂ ቦታ ተጫዋቾች በማሻገር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል ።
55ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ አጥቂው መሀመድኑር ናስር በደንብ ሳይደርስባት ቀርቷል ። ከ6 ደቂቃዎች በኋላም የጨዋታው ሁለተኛ ግብ ተቆጠረ በረከት ደስታ ከክንፍ ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ አለሙ በጭንቅላት ገጭቶቶ ግብ ጠባቂው ቢመልሰውም እዛው አካባቢ የነበረው በዛብህ መለዮ ኳሱን አግኝቶ በማስቆጠር የፋሲል ከተማን መሪነት ወደ 2 – 0 አሳደገ ።
እየተመሩ ያሉት ጅማ አባጅፋሮች በተቆጠሩባቸው ግቦች የደነገጡ በማይመስል መልከለ ኳሱን ተቆጣጥረው ግብ ለማግኘት ቢጥሩም የፋሲል ከተማ የተከላካይ መስመርን በቀላሉ ለማለፍ ተቸግረዋል ።
80ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅበብል የገቡት አፄዎቹ የጅማ አባጅፋር የተከላካይ ክፍልን ቅርፁን በማሳጣት በበዛብህ መለዮ አማካይነት ሶስተኛ ግብ አስቆጠሩ ።
ከ5 ደቂቃዎች በኋላ 85ኛ ደቂቃ ላይ ለአፄዎቹ የጨዋታውን የመጨረሻ ግብ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከአምሳሉ ጥላሁን በጥሩ ሁኔታ የደረሰውን ኳስ ማስቆጠር ቻለ ። ጨዋታውም በዚሁ የ 4 ለ 0 ውጤት ፍፃሜው ሆነ ። በዚህም መሰረት ፋሲል ከተማ በዘጠኝ ነጥቦች የሊጉ መሪ ሆኗል ።