በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንተ የመጨረሻ ጨዋታ ከዕረፍት በፊት 1 – 0 ሲመሩ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው በመቅረብ ባስቆጠሯቸው ሶስት ግቦች ወላይታ ድቻን 3 – 1 መርታት ችለዋል።
ፋሲል ከነማዎች በ20ኛው ሳምንት አዲስ አበባን በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ያሬድ ባየህን እና ሰይድ ሀሰንን በአምሳሉ ጥላሁን እና ሽመክት ጉግሳ ቀይረው ሲገቡ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በሳምንቱ ከሰበታ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በአበባየሁ አጂሶ ምትክ እንድሪስ ሰይድን አሰልፈዋል ።በምሽቱ ጨዋታ ላይ ወላይታ ድቻዎች በፋሲል ከነማ ላይ ጫና ፈጥረው በመጫወት የጀመሩት ሲሆን አፄዎቹ በአንድ ሁለት ቅብብል ኳሱን ይዘው ከሜዳቸው እንዳይወጡ በማገድ ረጃጅም ኳሶችን አንዲጠቀሙ ያስገደዷቸው ሲሆን በራሳቸው ሜዳ ላይ ተመቻቸው ኳሱን እንዳይዙ በፍጥነት ለመንጥቅ የተሳኩ ጥረቶችን ያደርጉ የነበረ ሲሆን የሚያገኟቸውን ኳሶችም በፍጥነት ወደ ፋሲል ከነማ የግብ ክልል ለማድረስ የሚሞክሩት ወላይታ ድቻዎች በተለይም በግራ መስመር በኩል ደጋግመው ወደ ፋሲል ከተማ ሳጥን ለመግባት ጥረቶቾን አድርገዋል ።
በግብ ሙከራዎች መታጀብ ያልቻለው ጨዋታ በ24ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚውን ግብ አስተናግዷል ። ቃልኪዳን ዘላለም ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው በረከት ወልደዮሀንስ በግንባር ግጭቶ በማስቆጠር ነበር የጦና ንቦቹን መሪ ማድረግ የቻለው ።ከግቡ በኋላ አፄዎቹ ቀድሞ ከነበረው በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢጥሩም የወላይታ ድቻዎች የማይቋረጥ ትኩረት በቀላሉ ኳሶችን መቀባበል እንዳይችሉ እና ወደ ጦና ንቦቹ ከመድረስ አግዷቸዋል ። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች መሪ ከሆኑ በኋላም ከመስመር ባደሉ እንቅስቃሴዎችቻቸው የአፄዎቹን የኋላ ክፍል ደጋግመው መፈተን ችለዋል ።
33ኛ ደቂቃ ላይ በፋሲል ከነማ በኩል በረከት ደስታ ከግቡ የቀኝ አቅጣጫ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ከግቡ ትይዩ የነበረው ሰይድ ሀሰን ሳይደርስበት ቀርቷል ።በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የጦና ንቦቹ በመከላከሉ ውጤታማ ጊዜን በማሳለፍ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርተው መውጣት ችለዋል ።በሁለተኛው አጋማሽ አፄዎቹ በተሻለ እንቅስቃሴ ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል መቅረብ የቻሉ ሲሆን ጠንከር ጠንከር ያሉ እና ፅዮን መርዕድን የፈተኑ የግብ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ46ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ፅዮን መርዕድ ያወጣው ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ስህተትን ተጠቀሞ ያገኘውን ኳስ ለውሳኔ በመዘግየቱ መልካሙ ቦጋለ ደርሶ አውጥቶበታል ።
በረከት ደስታም በ50ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ መምታት ቢችልም ፅዮን መርዕድ ተቆጣጥሮታል ።
የአፄዎቹ ተከታታይ ማጥቃት 60ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነቱን ግብ አስገኝቶላቸዋል ። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከበረከት ደስታ የደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ከነኳሱ በመዞር ወደ ግብ የመታው አስደናቂ ምት የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ መልካሙ ቦጋለ በራሱ መረብ ላይ አሳርፎታል ።ከግቡ መቆጠር ሶስት ደቂቃዎች በኋላ በዛብህ መለዮ ኦኪኪ አፎላቢ በደረቱ አብርዶ ያመቻቸለትን ኳስ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ግብ ጠባቂውን ማለፍ የቻለ አልነበረም ።
ወላይታ ድቻዎች በተፈጠረባቸው ጫና ወደ ኋላ ለማፈግፈግ የተገደዱ ሲሆን በ66ኛው ደቂቃ ላይም ደግሞ ሌላ ግብ አስተናግደዋል ። በረከት ደስታ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ከሱራፌል ዳኛቸው በረጅም የደረሰውን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ በመምታት ፋሲል ከነማን መሪ ማድረግ ችሏል ።ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ ወላይታ ድቻዎች ነቅለው በመውጣት ለማጥቃት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በተለይም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የጣሩ ቢሆንም ሳማኪን የፈተነ ከባድ ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም ።
የጦና ንቦቹ ለማጥቃት ወደ ፋሲል ከነማ የሜዳ ክፍል በርከት ብለው በተገኙበት ጊዜ ጊዜ ትተው የሄዱትን ቦታ በፈጣን ኳስ በመጠቀም አፄዎቹ ሶስተኛ ግባቸውን በኦኪኪ አፎላቢ አማካኝነት 80ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል ።በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ሌላ ግብ ሳይቆጠር ፋሲል ከነማ 3 ወላይታ ድቻ 1 ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 37 በማድረስ 2ኛ ደረጃን ሲያስጠብቅ ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ በነበረበት 3ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( ባህርዳር ) በመጪው ሚያዝያ 30 ( ዕሁድ ) ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ ወላይታ ድቻ ባህርዳር ከተማን ሲገጥም በቀጣዩ ቀን ግንቦት 1 ( ሰኞ ) ረፋድ 4 ሰዓት ጀምሮ ፋሲል ከነማ ሲዳማ ቡናን ይገጥማል ።