በ26ኛው ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከባህርዳር ከተማ አገናኝቶ ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት መልስ በተቆጠሩ ሁለት ሁለት ግቦች ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ25ኛው ሳምንት በፋሲል ከነማ 1 ለ 0 በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ አቤል ያለውን በተገኑ ተሾመ ተክተው ገብተዋል ። በባህርዳር ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ በሲዳማ ቡና 3 ለ 1 ሲረቱ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ለውጦችን በማድረግ ፋሲል ገብረሚካኤል ፤ መሳይ አገኘሁ ፤ ከሪም ኒኪማ እና አሊ ሱሌማንን በአቡበከር ኑሪ ፤ ሳለአምላክ ተገኝ ፤ ፍፁም አለሙ እና ግርማ ዲሳሳ ምትክ አሰልፈው ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረቶቸ ያደረጉበት ነበር ። የጨዋታው ቀዳሚ የግብ ሙከራም በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የተደረገ ሲሆን ፍሪምፖንግ ሜንሱ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የላከው ኳስ ወደ ግብነት ሳይቀየር ቀርቷል ።
- ማሰታውቂያ -
ከስደስት ደቂቃዎች በኋላም ላይ ኦሴ ማውሊ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ቻርለስ ሉክዋጎ አውጥቶበታል ።
ባህርዳር ከተማዎች በተሻለ ወደ ቅዱስጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶች ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን በተለይም በሁለቱ መስመሮች በኩል የተጋጣሚያቸውን ሳጥን ውስጥ ለመግባት ሲታትሩ ነበር ። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በአንድ ሁለት ቅብብሎች የባህርዳር ከተማ ተከላካዮችን አልፈው ለመሄድ ቢጥሩም እንቅስቃሴዎቻቸው የተሳኩ አልነበሩም ።
ከወሀ ዕረፍት መልስ 29ኛው ደቂቃ ላይ ያብስራ ተስፍዬ እና ሀይደር ሸረፋ ለመቀባበል በሚጥሩበት ጊዜ አለልኝ አዘነ ነጥቆ ለኦሴ ማውሊ ያቀበለውን ኳስ ማውሊ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት የቅዱስ ጊዮርጊስ መረብ ላይ አሳርፏል ።
ነገር ግን የጣና ሞገዶቹ መሪነት ብዙም የቆየ አልነበረም ። በባህርዳር ከተማ ሳጥን ውስጥ አሊ ሱሌማን በቸርነት ጉግሳ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አምበሉ ሀይደር ሸረፋ 36ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮታል ።
ከፍፁም ቅጣት ምቱ መሰጠት አንደ ደቂቃ ቀደም ብሎ ባህርዳር ከተማዎች ሁለተኛ ግብ የማስቆጠር ዕድል አግኝተው የነበረ ሲሆን ከሪም ኒኪማ በቀኝ አቅጣጫ ላይ ለኦሴ ማውሊ ያደረሰውን ኳስ አጥቂው ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ጨዋታው ወደ አቻ ውጤት ከተመለሰ በኋላ ባሉት ቀሪ የመጀመሪያው አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ቀድሞ ከነበረው ቀዝቀዝ ብሎ የተካሄደ ነበር ።
በአንፃራዊነት ፈረሰኞቹ ከተከላካዮች ጀርባ ለአጥቂዎቻቸው ኳሶችን ለማድረስ ቢጥሩም ፋሲል ገብረሚካኤልን የፈተነ የግብ ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በ1 – 1 ውጤት ተጠናቋል ።
ሁለተኛውን አጋማሽ ግርማ ዲሳሳን በመሳይ አገኘሁ ተክተው የገቡት ባህርዳር ከተማዎች ከግራ መስመር በኩል በሚነሱ ኳሰች የቅዱስ ጊዮጊስ የኋላ ክፍልን በመፈተን ነበር የጀመሩት ።
49ኛው ደቂቃ ላይ ማውሊ በጠንካራ ምት ወደ ግብ ለመሞከር ያደረገው ጥረት ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በቻርለስ ሉክዋጎ ተይዟል ።
በ54ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ ለመናፍ ዐወል ለማቀበል የሞከረውን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል አግኝቶ በቀኝ የሳጥኑ አቅጣጫ ገብቶ ለማስቆጠር ያደረገው ያደረገው ሙከራ ኳሱ ወደ ውጪ በመውጣቱ ሳይሳካለት ቀርቷል ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል 55ኛው ደቂቃ ሁለት ቅያሪዎች በመሀል ክፍል ላይ የተደረጉ ሲሆን ከነአን ማርክነህ እና ናትናኤል ዘለቀ ጋቶች ፓኖምን እና ያብስራ ተስፋዬ ተክተው ገብተዋል ። ከቅያሪዎቹ በኋላም ፈረሰኞቹ በአጋማሹ ቀደም ብለው ከነበሩት ደቂቃዎች በተሻለ ጫናን በመፍጠር ወደ ተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል በመድረስ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።
57ኛው ደቂቃ ላይ ሳይታሰብ ሄኖክ አዱኛ ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ፋሲል ገብረሚካኤል መልሶቶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሱሌማን ሀሚድ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ያሻገረው ኳስ ያገኘው ከነአን ማርክነህ ኳሱን ተረጋግቶ በመቆጣጠር ወደ ግብ በመላክ ከመረብ ላይ አሳርፎ ፈረሰኞቹን ከመመራት ወደ መሪነት መቀየር ችሏል ።
ከግቡ በኋላ ፈረሰኞቹ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወት የሚገኙ ኳሶቾን በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወደ ባህርዳር ከተማ የሜዳ ክፍል በማድረስ ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በአንፃሩ በባህርዳር ከተማ በኩል በተሻለ ኳሱን ይዘው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገው ነበር ።
በ74ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረሚካኤል አለሙ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ሉክዋጎ በቀላሉ ተቆጣጥሮታል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ግርማ ዲሳሳ በግራ አቅጣጫ ወደ ሳጥን ለመግባት በሚጥርበት ጊዜ በአቤል ያለው በተሰራበት ጥፋት የጣና ሞገዶቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል ።
የመጀመሪያው ግብ አስቆጣሪ ኦሴ ማውሊም የፍፁም ቅጣት ምቱን ከቻርለስ ሉክዋጎ በተቃራኒ አቅጣጫ በመምታት ከመረብ አሳርፎ የጨዋታውን ውጤት ወደ 2 ለ 2 ቀይሮታል ።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ ዳግም ጫን ብለው ለመጫወት የጣሩ ሲሆን በተለየም በሄኖክ አዱኛ አማካኝነት ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል በሚሻገሩ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በ2 ለ 2 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ይህንንም ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 55 በማድረስ በመሪነቱ ሲቀጥል ባህርዳር ከተማ በበኩሉ በ30 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል ።
በ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 11 ( ቅዳሜ ) ረፋድ 4:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልቂጤ ከተማ ሲጫወት በዕለቱ 10 ሰዓት ላይ ደግሞ ባህርዳር ከተማ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማል ።