የ18ኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጅማሮውን በዛሬው ዕለት ሲያደርግ አስገራሚ ጨዋታ አስመልክቶናል ። አህመድ ሁሴን ሀትሪክ በሰራበት እና በ72ኛ ደቂቃ ተጎድቶ በወጣበት ጨዋታ አዞዎቹ እስከ 80ኛው ደቂቃ 4 – 1 ሲመሩ ቢቆዩም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠሩባቸው ሶስት ግቦች ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል ።
ሀድያ ሆሳዕና በ17ኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ የገቡ ሲሆን ኡመድ ኡክሪ በሀብታሙ ታደሰ ምትክ ሲያስገቡ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ አዲስ አበባ ከተማን ሲረቱ በነበረው ምርጥ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳናደርጉ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎውች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ጥሩ አጀማመር ማድረግ ቢችሉም ቀድመው ነበር ግብ ያስተናገዱት ። በ17ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ሙና በቀለ ወደ ግብ ሲያሻግረው ኳሱን ግብ ጠባቂው መመለስ ቢችልም የተመለሰው ኳስ በኡቸና ማርቲን አቀባይነት እና አህመድ ሁሴን ጨራሽነት ግቡ ተቆጥሯል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በመስመር በኩል ለማድረግ ያሰቧቸው እንቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው በመገታቱ ወደ ግብ ቀርበው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ። የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውንም በ21ኛው ደቂቃ ላይ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ግርማ በቀለ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በሳምሶን አሰፋ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
- ማሰታውቂያ -
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ አሸናፊ ፊዳ ኳሱን ከራሱ የሜዳ ክፍል ለማራቅ በረጅም የመታው ኳስ በአህመድ ሁሴን ተይዞ ኳሱ የተመቻቸለት ፀጋዬ አበራ ኳሱን በግሩም ሁኔታ ከመረብ በማሳረፍ የአዞዎቹን መሪነት ወደ 2 – 0 ከፍ አደረገ ።ወደ ሀድያ ሆሳዕና ሳጥን መግባት ተቸግረው የቆዩት አርባምንጭ ከተማዎች በ30ኛው ደቂቃ ላይ በኡመድ ኡክሪ አማካኝነት ይዘው የገቡት ኳስ በኡቸና ማርቲን በእጅ መንካቱን ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ወደ 2 – 1 መቀየር ችሏል ።
ከፍፁም ቅጣት ምቱ መቆጠር ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን እና ኡመድ ኡክሪ ያደረጉት ጥሩ ቅብብል በሳጥን ውስጥ በግብ አስቆጣሪው ቢሞከርም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ። በአርባምንጭ ከተማ በኩም በ35 እና 36ኛ ደቂቃ ላይ በአቡበከር ሻሚል እና አህመድ ሁሴን ከሳጥን ውጪ ያደረጉት የግብ ሙከራ በግብ ጠባቂው ያሬድ የተያዘ ሲሆን በ45+2 ደቂቃ ላይም ሙና በቀለ ከቅጣት ምቴ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ዘቡ ዳግም ከተመለሰ በኋላ የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቋል ።
ሁለተኛውን አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች በጥሩ መነቃቃት እና የተጋጣሚያቸውን የተከላካይ ክፍል በማስጨነቅ ነበር የጀመሩት ። በዚህም በ54ኛው ደቂቃ ላይ በላይ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ያሬድ ሲመለስ በቅርብ የነበረው አህመድ ሁሴን አግኝቶ ወደ ግብ በመምታት ማስቆጠር ችሏል ።
ከግቡ በኋላ አዞዎቹ ወደ ኋላ በማፈግፈግ እና በፈጣን ኳሶችን ወደ ፊት በማድረስ ለማስቆጠር ጥረቶችን በማድረግ እንዲሁም በሀድያ ሆሳዕና በኩል ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የአርባ ምንጭ ከተማን የኋላ መስመር ሰብረው ለመግባት ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ችለዋል ። ነገር ግን 64ኛው ደቂቃ ላይ በአርባ ምንጭ ከተማ በኩል የተቆጠረው ግብ ጨዋታው የተጠናቀቀ እንዲመስል አደርጎታል ። ሙና በቀለ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባር ገጭቶ ለማውጣት ሲሞክር ኳሱን ሳጥን ውስጥ ሆኖ ያገኘው በላይ ገዛኸኝ ወደ ግብ ሞክሮት ልክ እንደ ሶስተኛው ጎል ሁሉ በቅርብ የነበረው አህመድ ሁሴን በማስቆጠር ለክለቡ አራተኛ ለራሱ ደግሞ ሶስተኛ ግብ ከመረብ አሳረፈ ። ሀትሪክ የሰራው አህመድ ከሶስተኛው ግቡ በኋላ ሜዳ ውሰጥ መቆየት የቻለው ለስምንት ደቂቃዎች ብቻ የነበረ ሲሆን በፍሬዘር ካሳ በሰራበት ጥፋት ተጎድቶ ከሜዳ ወጥቷል ።
ከ80ኛው ደቂቃ በኋላ የነበሩች የጨዋታው ደቂቃዎች ለሀድያ ሆሳዕና ልዩ የነበሩ ለአርባምንጭ ደግሞ የቅዠት ደቂቃዎች ነበሩ ። በ80ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሀብታሙ ታደሰ ከብርሀኑ በቀለ የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባጠበበበት በኩል መቶ ማስቆጠር ችሏል ። ግቡን ረዳት ዳኛው ሽረውት የነበረ ቢሆንም ከመሀል ዳኛው ጋር ከተናጋገሩ በኋላ ግቡ ፀድቋል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በግቡ ተነቃቅተው ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር የአዞዎቹን በር ማንኳኳት የቀጠሉ ሲሆን በ88ኛው ደቂቃ ላይም የቡድኑ አምበል ሄኖክ አርፊጮ ለሀብታሙ ታደሰ የሰጠውን ኳስ መልሶ በመቀበል የነብሮቹን ሶስተኛ ግብ አስቆጠረ ። የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች መነቃቃት የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች ድናጋጤ የጨዋታውን የመጨረሻ ደቂቃዎች እጅግ አጓጊ አድርገውት ነበር ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች የደቂቃው መሄድ ሲያስጨንቃቸው አርባምንጭ ከተማዎች ደግኖ ቶሎ ባለቀ ብለው በሚጠብቁት ሰዓት 90+2 ደቂቃ ላይ የሀድያ ሆሳዕናው ብርሀኑ በቀለ ከሳጥኑ ውጪ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ በሳምሶን አሰፋ መረብ ላይ አረፈ ። ሀድያ ሆሳዕና 4 አርባምንጭ ከተማ 4 የጨዋታው የመጨረሻ ውጤትም እንዲህ ሆኖ ተጠናቀቀ ።
ከጨዋታው አንድ አንድ ነጥብ ይዘው የወጡት ሁለቱም ክለቦች በደረጃቸው ላይ ለውጥ ያላመጡ ሲሆን ነጥባቸውን ግን 22 ( ሀድያ ሆሳዕና ) እና 23 ( አርባምንጭ ከተማ ) ማድረስ ችለዋል ።
በ19ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕና በመጪው ማክሰኞ ቀን 9 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማን ሲገጥም አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በማግስተሐ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ባህርዳር ከተማን ይገጥማል ።