በ22ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ በመጨረሻ የተደረገው እና 10 ሰዓት ላይ የጀመረው የሀድያ ሆሳዕና እና መከላከያ ጨዋታ ልክ እንደ ዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ውጤት 2 – 1 የተጠናቀቀ ሲሆን የጨዋታው አሸናፊ ደግሞ መከላከያ ሆኗል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በ21ኛው ሳምንት ከአዲስ ከበባ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ሁለት ለውጦቶችን በማድረግ ፍቅረየሱስ ተክብርሀንን እና ኤፍሬም ዘካርያስን በአበባየሁ ዮሀንስ እና ሳምሶን ጥላሁን ምትክ ሲያሰልፉ መከላከያዎች ደግሞ በሳምንቱ ኢትዮጵያ ቡናን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን በክሌመንት ቦዬ ፤ አሚን ነስሩ እና ገናናው ረጋሳ ምትክ ሙሴ ገብረኪዳን ፤ አሌክስ ተሰማ እና ዳዊት ማሞ ጨዋታውን ጀምረዋል ።የሀድያ ሆሳዕና እና መከላከያ ጨዋታ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን በማድረግ የጀመሩት ነበር ።
በጥሩ ፉክክር የተጀመረው ጨዋታም ቀዳሚውን ግብ በ9ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ያስመለከተን ። እስራኤል እሸቱ ከቢንያም በላይ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ወደ ግብ በመምታት መከላከያን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ጫና ፈጥረው በመጫወት የመከላከያን የኋላ ክፍል አልፈው ግቦችን ለማስቆጠር በተወሰኑ አጋጣሚዎች ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ። የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውንም በ29ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉ ሲሆን ኡመድ ኡክሪ በቀኝ መስመር አቅጣጫ የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በያሬድ ቦጋለ ድኖበታል ።
መከላከያዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው የሀድያ ሆሳዕናን የኳስ ሂደት በመግታት የሚገኙ ኳሶችን በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ለመድርስ ጥረቶችን አድርገው ነበር ። የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ሀብታሙ ታደሰ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ያገኘውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ቢጠበቅሞ የሀብታሙ ኳስ ጠንካራ ባለመሆኑ ሙሴ ገብረኪዳን በቀላሉ ይዞታል ።በሁለተኛው አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎች ይበልጥ ተጠናክረው ገብተው የአቻነቱን ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉ ቢሆንም አጋማሹ በተጀመረ አስረኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል ። የመጀመሪያው ግብ ሲቆጠር አመቻችቶ ያቀበለው ቢንያም በላይ በዚህ አጋጣሚ ላይ ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ አዲሱ አቱላ 56ኛው ደቂቃ ላይ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የመከላከያን መሪነት ወደ 2 – 0 ከፍ ማድረግ ችሏል ።ሀድያ ሆሳዕናዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ላይ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም የመከላከያን የኋላ ክፍል ሰብረው በመግባት የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ቆይተው ነበር ። በ75ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሀድያ ሆሳዕናዎች የመጀመሪያውን ግብ አግኝተዋል ።
- ማሰታውቂያ -
ሀብታሙ ታደሰ ከተስፋዬ አለባቸው የደረሰውን ኳስ ተረጋግቶ ወደ ግብ በመምታት በሙሴ ገብረኪዳን መረብ ላይ አሳርፏል ።በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ጫናቸውን በማጠናከር ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ያደረጓቸው ሙከራዎች ፍሬያማ ሳይሆኑ ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ በ27 ነጥብ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ በ29 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 3 ( ረቡዕ ) ረፋድ 4:00 ጀምሮ ሀድያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም ግንቦት 5 ( አርብ ) በተመሳሳይ 4:00 ጀምሮ መከላከያ ከሲዳማ ቡና ጋር ጨዋታውን ያደርጋል ።