ስድስት ያህል ግቦች በተስተናገዱበት የ11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር በእዮብ አለማየሁ እና መሀመድኑር ናስር ሁለት ሁለት ግቦች ታግዞ ሀድያ ሆሳዕናን 4 ለ 2 በማሸነፍ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አስመዝግቧል ።
ሀድያ ሆሳዕና በ10ኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ የሶስት ተጫዋቾች ቅያሪ አድርገው የገቡ ሲሆን በፍሬዘር ካሳ ፣ እሸቱ ግርማ እና ፍቅረየሱስ ተክለ ብርሀን ምትክ ቃልዓብ ውብሸት ፣ ኤልያስ አታሮ እና አበባየሁ ዮሐንስ ወደ ሜዳ ገብተዋል ። በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ባሳኩበት ጨዋታ ወደ ሜዳ ከገባው ምርጥ አስራ አንድ አራት ተጫዋቾችን የቀየሩ ሲሆን በአላዛር ማርቆስ ፣ ሽመልስ ተገኝ ፣ ሙሴ ከበላ እና ዳዊት ፍቃዱ ቦታ ዮሀንስ በዛብህ ፣ እያሱ ለገሰ ፣ ዱላ ሙላቱ እና በላይ ዓባይነህ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
ገና ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴ ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል በቶሎ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስም የቻሉበት ነበር ። በዚህም በመጀመሪያዎቹ 18 ደቂቃዎች ውስጥ 3 ግቦችን ለመመልከት አስችሎናል ።
- ማሰታውቂያ -
በ5ኛው ደቂቃ ላይ በጅማ አባጅፋር በኩል የተገኘውን የማዕዘን ምት ዱላ ሙላቱ አሻግሮ በሀድያ ሆሳዕና ተጫዋች ተገጭቶ ሲመለስ ያገኘው እዮብ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ጅማ አባጅፋርን ቀዳሚ አደረገ ። ግቡ ከተቆጠረ ባሉ ሁለት ደቂቃዎች ውስጥም ጅማ አባጅፋሮች በእዮብ አለማየሁ እና በተስፋዬ መላኩ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን አምክነዋል ።
10ኛው ደቂቃ ላይ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ብርሀኑ በቀለ ከቀኝ መስመር ተነስቶ ወደ ግብ ያደረገው ምርጥ ሙከራ በግብ ጠባቂው ዮሐንስ በዛብህ ተመልሷል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ሀድያ ሆሳዕናዎች አቻ የሚሆኑበትን ግብ አግኝተዋል ። የጅማ አባጅፋር ተጫዋቾች ኳሱን ከግብ ክልል በደንብ ማራቅ ባለመቻላቸው ሀብታሙ ገዛኸኝ የነጠቀውን ኳስ ለባዬ ገዛኸኝ አቀብሎት ባዬ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ሲመለስ የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ ወንድማገኝ ማርቆስ በራሱ ላይ አስቆጥሮታል ።
የሀድያ ሆሳዕና የአቻነት ግብ ከተገኘች ብዙም ሳይቆይ 18ኛ ደቂቃ ላይ መሀመድኑር ናስር ሶሆሆ ሜንሱ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ በማስቆጠር ጅማ አባጅፋርን ዳግም መሪ አደረገ ።
የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች በተለይም በቀኝ መስመር በኩል ሰብረው በመግባት እና በሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት ያደረጓቸው ጥረቶች በመከላከሉ ጥሩ በነበሩት ጅማ አባጅፋሮች በተደጋጋሚ ከሽፎባቸዋል ። በጅማ አባጅፋር ተጋጣሚያቸው ኳሱን መስርቶ እንዳይወጣ ጫና በማድረግ እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን 21ኛ ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ በግብ ጠባቂው የተያዘበት እና 35ኛ ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ ለዚህ ማሳያ ነበሩ ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በጅማ አባጅፋር የ2 ለ 1 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ በመመራት ላይ የነበሩት ሀድና ሆሳዕናዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት በመሄድ ለማጥቃት አስበው የገቡ ቢመስልም ጠንካራ የነበረውን የጅማ መከላከል ሰብረው ለመግባት ተቸግረዋል ። በጅማ አባጅፋር በኩል በራሳቸው ሜዳ በርከት ብለው በመገኘት እና የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ በመላክ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።
65ኛ ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት መሀመድኑር ናስር ይዞ የሄደው ኳስ በመስዑድ መሀመድ እና ዳዊት እስጢፋኖስ በኩል አልፎ በእዮብ አለማየሁ ተቆጥሯል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በላይ ዓባይነህ ከቅጣት ወደ ግብ የላከው ኳስ በሶሆሆ ሜንሱ ተጨርፎ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች ምንም እንኳን ኳሱን መያዝ እና አብዛኛውን ጊዜ በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል ማሳለፍ ቢችሉም የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን በጣም ተቸግረው ነበር ።
በ73ኛ ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ያቀበለውን ኳስ የግብ ጠባቂውንም ከግቡ መውጣት ተመልክቶ መሀመድኑር ናስር በግሩም ሁኔታ የጅማ አባጅፋርን 4ኛ ግብ አስቆጠረ ። የግብ ልዩነቱን ለማጥበቅ ጥረታቸውን የቀጠሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች 90ኛ ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል ። ተቀይሮ የገባው ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በሳጥኑ በግራ አቅጣጫ ሆኖ የደረሰውን ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት ኳስን ከመረብ አገናኝቷል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላ የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ ሚካኤል ጆርጅ ላይ በሰራው ጥፋት ምክንያት ለሀድያ ሆሳዕና የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠ ። ነገር ግን በአምበሉ ሄኖክ አርፊቹ የተመታው የፍፁም ቅጣት ምት የግቡን ቋሚ መቶ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
አምስት ያህል ተጨማሪ ደቂቃዎች የነበሩት ጨዋታ በስተመጨረሻም ጅማ አባጅፋርን አሸናፊ በማድረግ ተጠናቀቀ ። ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር ነጥቡን 7 ማድረስ የቻለ ቢሆንም ባለበት የግብ ዕዳ( – 9 ) ምክንያት በደረጃው ላይ ለውጥ ያላደረገ ሲሆን የተሸነፈው ሀድያ ሆሳዕና በ13 ነጥብ ባለበት የ11ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ሲዳማ ቡናን እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ ሰበታ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።