የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከሰበታ ከተማ አገናኝቶ በሳምሶን ጥላሁን ብቸኛ የፍፁም
ቅጣት ምት ግብ ሀድያ ሆሳዕና 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
ሀድያ ሆሳዕና በ11ኛ ሳምንት ጨዋታ በጅማ አባጅፋር በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን ሶሆሆ ሜንሳህ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ አበባየሁ ዮሀንስን እና ሀብታሙ ታደሰን በመሳይ አያኖ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን እና ሚካኤል ጆርጅ የቀየሩ ሲሆን በሰበታ ከተማ በኩልም በፋሲል ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ አራት ተጫዋቾችን በመለወጥ የገቡ ሲሆን በለአለም ብርሀኑ ፣ ጌቱ ሀይለማርያም ፣ ታፈሰ ሰርካ እና አብዱልፊዝ ቶፊቅ ምትክ ሰለሞን ደምሴ ፣ ዘላለም ኢሳያስ ፣ በሀይሉ ግርማ እና ፍፁም ገብረማርያም ጨዋታውን መጀመር ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቶሎ ቶሎ ከመቀማማት አልፎ የግብ ሙከራዎችን በስፋት ያላስመለከተን ነበር ። በ3ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬዘር ካሳ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
በ20ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ዘካርያስ ፍቅሬ ወደ ግብ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ሰለሞን አያኖ ተመልሶ ሲወጣ በድጋ የተገኘው የማዕወን ምትም ተሻምቶ ፍፁም ገብረማርያም አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ሰለሞን አያኖ በድጋሚ አድኖታል ። መደበኛው የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 4 ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩች ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ተጨራርፎ ለግቡ በቅርበት ሆኖ ዘካርያስ ፍቅሬ የመታው ኳስ ከግቡ አግዳሚ በላይ ሊወጣ ችሏል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ፊት በመሄድ የተሻሉ ሆነው የታዩበት ሲሆን ከአጋማሹ መጀመር 10 ደቂቃዎች በኋላ ግብ ማግኘት ችለዋል ። ከመስመር የተሻገረን ኳስ አለማየሁ ሙለታ በሳጥን ውስጥ ሆኖ በአጅ መንካቱን ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕናዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ለአጋጣሚው መፈጠር መንስኤ የነበረው ሳምሶን ጥላሁን አስቆጠረ ።
ከግቡ በኋላ የሀድያ ሆሳዕና ማጥቃት የቀጠለ ሲሆን ሰበታ ከተማዎች በተሻለ ወደፊት ለመጓዝ የጨዋታውን የመጨረሻ ደቂቃዎች ጠብቀው ነበር ። ነገር ግን ያን ያህል ግብ ጠባቂውን የፈተነ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ነበር ጨዋታው ፍፃሜውን ያገኘው ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 16 በማድረስ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሰበታ ከተማ በ7 ነጥብ ባለበት 15 ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በ13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕና ቅዱስ ጊዮርጊስን ሰበታ ከተማ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።