የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ አገናኝቶ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በተቆጠሩ ግቦች ሀዋሳ ከተማዎች 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንዋል ።
ሀዋሳ ከተማ በ10ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ያደረጉ ሲሆን በአብዱልባሲጥ ከማል ምትክ ዳዊት ታደሰን ጨዋታውን አንዲጀምር ሲያደርጉ በድሬዳዋ ከተማ በኩል ደግሞ መከላከያን ከረቱበት ጨዋታ የሶስት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ዓወት ገብረሚካኤልን ፣ ቢንያም ጥዑመልሳንን እና አብዱለጢፍ መሀመድን በእንየው ካሳሁን ፣ አብዱልፈታ አሊ እና ማማዱ ሲዲቤን ተክተው አስገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በደጋፊዎቻቸው ፊት የተጫወቱት ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት በመውሰድ የተጫወቱ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በፈጣን ሽግግሮች በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በጠንካራ የግብ ሙከራዎች ያልታጀበው ጨዋታ 17ኛ ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግዷል ። ዓወት ገብረሚካኤል ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አብዱራህማን ሙባረክ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከውን ኳስ መድኃኔ ብርሀኔ በራሱ ላይ አስቆጥሮ ድሬዳዋ ከተማዎች መሪ መሆን ችለዋል ።
በመመራት ላይ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ከግቡ በኋላ ቀድሞ ከነበራቸው በተሻለ ወደ ፊት መሄድ የቻሉባቸው አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል ። በዚህም 25ኛ ደቂቃ ላይ ወንድማገኝ ሀይሉ ከበቃሉ ገነነ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችሏል ።
በአንድ አቻ ውጤት የቀጠለው ጨዋታ በጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን በሁለቱም በኩል ቀድሞ ሁለተኛውን ግብ ለማግኘት የተደረጉት ጥረቶች ሳይሳኩ የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ በሀዋሳ ከተማ የማጥቃት የበላይነት የተጀመረ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማዎችም በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን እንቅስቃሴ እና በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ቢያደርጉም ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን በማድረጉ ረገድ በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ደከም ብለው ታይተዋል ።
በ80ኛ ደቂቃ ላይ መሳይ ጳውሎስ በረጅም ያሻገረውን ኳስ ፀጋሰው ድማሙ ለማውጣት ያደረገው ሙከራ በአግባቡ ሳይደረግ ቀርቶ ኳሱ የደረሰው አብዱለጢፍ መሀመድ ድሬዳዋ ከተማን ዳግም መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል ። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች በመስፍን ታፈሰ ግሩም ግብ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ተጭነው የተጫወቱት በዘርዓይ ሙሉ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በመስፍን ታፈሰ አማካኝነት የፈጠሩት ሌላ የግብ ዕድል በግቡ ቋሚ ተመልሶ ወጥቷል ።
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ቸርነት ዐወሽ ከማዕዘን የተነሳን ኳስ ተጠቅሞ ባስቆጠረው ግብ ሀዋሳ ከተማዎች አሸናፊ መሆን ችለዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 20 በማድረስ ወደ 3ኛ ደረጃ ሲመለስ ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በ14 ነጥብ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል ።
በ12ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ባህርዳር ከተማን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አርባምንጭ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።