በሊጉ የ25ተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ በሁለት ነጥብ ተበላልጠዉ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በቡናማዎቹ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በድል ከተወጡ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና ከደረሰባቸዉ ሽንፈት ለማገገም በብዙ መንገድ ለዉጥ አድርገዉ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በአንፃሩ በሃዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ ከአምስት ተከታታይ ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ በ24ተኛዉ ሳምንት ያገኙትን ድል ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ቡናማዎቹ ባለፈው ሳምንት ከተጠቀሟቸዉ ተጫዋቾች በጉዳትም በቅጣትም ምክንያት በርከት ያለ ለዉጥ አድርገዉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች በ24ኛ ሳምንት ጨዋታ ከተጠቀሟቸዉ ተጫዋቾች አንድ ለዉጥ ብቻ አድርገዉ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
- ማሰታውቂያ -
እንደወትሮው ሁሉ በኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቅብብል እና የጨዋታ የበላይነት የጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምንም እንኳን ቡናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ቢይዙም በሀዋሳ ከተማዎች በኩል ደግሞ ለተጋጣሚ ቡድን ክፍተቶችን በመዝጋት እና ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገው በመጫዎት በመሀል በመሀልም የሚገኙ ኳሶችን በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል።
በዚህ ሂደት ለ15 ደቂቃዎች ያክል የቀጠለዉ ጨዋታም በ17ኛዉ ደቂቃ ላይ ጥሩ የምትባል የግብ ሙከራን አስመልክቶናል። ወጣቱ የቡና ተከላካይ ከርቀት ወደ ግብ የላካትን ኳስ የሀዋሳዉ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ እንደምንም ተቆጣጥሯታል።
ከዚች ድንቅ ሙከራ በኋላ ምንም እንኳን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢኖራቸዉም ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ቡናዎች በ27ኛዉ ደቂቃ ላይ በድጋሚ በአብነት ደምሴ አማካኝነት ከርቀት ለግብ የቀረበች ሙከራ አድርገዋል።
በጨዋታው ይበሌጥኑ በጥንቃቄ ሲጣወቱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በአንፃሩ በ34ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል።
ሄኖክ ድልቢ ያሻገረለትን ኳስ ብሩክ በየነ ከተከላካዩ ገዛኸኝ ደሳለኝ ጋር እንደምንም ታግሎ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሯታል። ሆኖም ግን የሀዋሳዎች መሪነት የዘለቀዉ ለ5 ደቂቃዎች ብቻ ነበር በቀኝ መስመር በኩል በተሰራ ጥፋት የተገኘዉን የቅጣት ምት አላዛር ሽመልስ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ሆኖ የመጀመሪያዉን አጋማሽ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ መንገድ የቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በ56ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ተጨማሪ ግብ ተስተናግዷበታል። ከአቤል እንዳለ የተሻገረለትን ኳስ እንዳለ ደባልቄ ለሞቆጣጠር ሲሞክር ኳሷ ተጨርፋ ግብ ጠባቂዉን ዳግም ተፈራን ነክታ ወደ ግብነተ ተቀይራለች።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ተጭነዉ መጫወት የጀመሩት ሀዋሳዎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ ይባስኑ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል።
በ82ኛዉ ደቂቃ ላይ በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ አላዛር ሽመልስ ላይ ቸርነት አዉሽ ጥፋት በመስራቱ ምክንያት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹ ለተቀናጁት ጣፋጭ ድል ሶስተኛዋን ግብ ማሴቆጠር ችሏል።ዉጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና በ37 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በ36 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በቀጣይ ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ የሚገናኙ ይሆናል።