በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማሮውን በዛሬው ዕለት ሲያደርጉ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩትን ሀዋሳ ከተማን እና ፋሲል ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ታይቶበት በሀይቆቹ 2 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ13ኛው ሳምንት ጨዋታ በባህርዳር ከተማ 2 ለ 0 የተሸነፉት ሀዋሳ ከተማዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ሶስት ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን ፀጋሰው ድማሙ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግን እና ተባረክ ሄፌሞን በአዲስአለም ተስፋዬ ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና ብሩክ በየነ የተኩ ሲሆን በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ ከአዳማ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ ከነበረው ቋሚ 11 ሶስተ ቅያሪ በማድረግ በሰይድ ሀሰን ፣ በአምሳሉ ጥላሁንን እና በሀብታሙ ተከስተ ምትክ ያሬድ ባየህን ፣ ሳሙኤል ተስፋዬን እና አለምብርሀን ይግዛውን በጨዋታወሸ አሰልፈዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በተለይም እስከ ውሀ እረፍት ድረስ በሁለቱም በኩል በፈጣን እንቅስቃሴዎች ወደ ግብ የመድረስ ፍላጎቶች የተስተዋሉበት ሲሆን ምንም እንኳክ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ወደ ግብ እንዲቀርቡ ባያደርጋቸውም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በሀዋሳ ከተማም ሆነ በፋሲል ከተማ ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
24ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ኳሱን ከግብ ክልላቸው ለማራቅ ሲሞክሩ ያገኘው ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ። 28ኛ ደቂቃ ላይ የአፄዎቹ የግራ መስመሬ ተጫዋች ሳሙኤል ተስፋዬ መጎዳቱን ተከትሎ አምሳሉ ጥላሁን ተክቶት ሊገባ ችሏል ። አፄዎቹ አምሳሉ ወደ ሜዳ ተቀይሮ ከገባ በኋላ በግራ መስመር በኩል በተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ ነበር ።
32ኛው ደቂቃ ላይ አለምብርሀን ይግዛው በፍጥነት ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለኦኪኪ ቀንሶለት የነበረ ቢሆንም አጥቂው የደረሰውን ኳስ ሊጠቀምበት አልቻለም ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ተባረክ ሄፌሞ በቀኝ መስመር በኩል በጥሩ እንቅስቃሴ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ አጨራረሱን ሳያሳምር ቀርቷል ።
ከውሀ እረፍት በኋላ በተወሰነ መልኩ የተቀዛቀዘው ጨዋታ ግብ ሳያስተናግድ ነበር የመጀመሪያውን አጋማሽ ያጠናቀቀው ።
ሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ እንቅስቃሴ የጀመሩት ሀይቆቹ መስፍን ታፈሰን ኢላማ ያደርጉ ኳሶችን በተደጋጋሚ ወደ አፄዎቹ የግብ ክልል ምድረስ የቻሉበትም ነበር ። 60ኛው ደቂቃ ላይ በግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ በረጅም የተመታው ኳስ በመስፍን ታፈሰ በጭንቅላት ከተገጨ በኋላ ኳሱ የደረሰው ከድር ኩሊባሊ የግብ ጠባቂውን መውጣት ሳይመለከት ወደ ኋላ ለማቀበል ሲሞክር ግቡን ለቆ የወጣውን ሚካኤል ሳማኪን አልፎ ኳስ እና መረብ ተገናኛቷል ።
ሀዋሳ ከተማዎች ከመጀመሪያው ግብ መቆጠር በኋላ በፈጣን እንቅስቃሴ በ61 እና 63ኛ ደቂቃ ላይ በተባረክ ሄፌሞ አማካኝነት ያገኟቸውን ሁለት የግብ ዕድሎች ሳይጠቀሙ ቀርተዋል ።
ቀድሞ ግብ የተቆጠረባቸው ፋሲል ከተማዎች ፍቃዱ አለሙን እና ሰይድ ሀሰንን በሱራፌል ዳኛቸው እና አለምብርሀን ይግዛው ቀይረው አስገብተዋል ። ከቅያሪዎቹ በኋላ ብልጫውን ወስደው መጫወት የቻሉት አፄዎዎቹ የሀዋሳ ከተማን የተከላካይ መስመር መፈተን ችለው ነበር ። 68ኛ ደቂቃ ላይ የሁለቱ ቅያሪዎች ጥምረት ለፋሲል ከተማ ግብ ያስገኘ ሲሆን ከሰይድ ሀሰን የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ፍቃዱ አለሙ አፄዎቹን አቻ ማድረግ የቻለበትን ግብ አስቆጠሯል ።
አፄዎቹ አቻ የሆኑበትን ግብ ካገኙ በኋላ ሌላ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በኦኪኪ አፎላቢ እና በያሬድ ባነህ አማካኝነት ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በመሀመድ ሙንታሪ ተይዘዋል ። 78ኛ ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ለፍቃዱ አለሙ ያቀበለው ነፃ ኳስ ግብ ሆነ ተብሎ ሲጠበቅ ፍቃዱ ኳሱን በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ግብ ጠባቂው ወጥቶ ኳሱን ይዞበታል ።
የአፄዎቹ ጫና የበረታባቸው ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጫወት ተገደው ነበር ። 85ኛ ደቂቃ ላይ የጨዋታውን ውጤቶ የቀየረ ግብ ተቆጠረ ። ሽመከሰል ጉግሳ ከማዕዛን ተሻገረለትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢሞክሮት የግቡን ቋሚ ለትሞ የተመለሰ ሲሆን የተመለሰውን ኳስ ባሳለፍነው የውድድር አመት የሊጉ ኮከብ ታዳጊ ተጫዋች ሽልማትን ያሸነፈው ወንድማገኝ ሀይሉ በራሱ ጥረት ይዞት የሄደውን ኳስ በምርጥ አጨራረስ ግብ ማድረግ ችሏል ። ግቡም ሀዋሳ ከተማን አሸናፊ አድርጎ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 23 በማድረስ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ፋሲል ከተማ በበኩሉ የዛሬውን ሽንፈት ተከትሎ በ22 ነጥብ ወደ 3ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።
በ14ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ መከላከያን ፋሲል ከተማ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል ።