በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 – 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል ።
ሀዋሳ ከነማዎች በ20ኛው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆኖ ዳግም ተፈራን ፤ ዳንኤል ደርቤን ፤ ሔኖክ ድልቢን እና መስፍን ታፈሰን በመሃመድ ሙንታሪ ፤ ፀጋሰው ድማሙ ፤ ኤፍሬም አሻሞ እና ዳዊት ታደሰ ምተክ ሲያሰልፉ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በሳምንቱ ሲዳማ ቡናን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ በሱሌማን ሀሚድ እና ሀይደር ሸረፋ ምትክ ደስታ ደሙን እና ከነአን ማርክነህን አሰልፈዋል ።ጨዋታውን ፈረሰኞቹ ቶሎ ቶሎ ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል በመድረስ የጀመሩት ነበር ። በዚህም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ፍሪምፖንግ እና ከነአን ማርክንህ ወደ ግብ ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው ።
በሁለቱም መስመሮች በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የጣሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ17ኛው ደቂቃ ላይ ግቦ አስቆጥረዋል ። በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ የቆሙ ኳሶችን መጥኖ ለቡድን አጋሮቹ ግብ ማስቆጠር ትልቅ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ከነአን ማርክነህ ፈረሰኞቹን ቀዳሚ አድርጓል ።ከግቡ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች በተውነ የተነቃቁ ቢመስሉም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ክልል ተጠግተው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ አልቻሉም ነበር ። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ ከግቡ በኋላ ኳሱን ይዘወ በመጫወት የተጋጣሚያቸውን ጫና መቀነስ ችለዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ሜዳ መግባት ቢችሉም በውድድር አመቱ ካደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 7 ግብ ብቻ ያስተናገደውን የቅዱስ ጊዮርጊስ የኋላ ክፍል ለማስከፈት ተቸግረዋል ። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ የሚገኙ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በማድረስ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት በ54ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። ቸርነት ጉግሳ በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ በተነጠቀበት ጊዜ ቅርብ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ወደ ግብነት ቀይሮታል ።
- ማሰታውቂያ -
ከሁለተኛው ግብ በኋላ ፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥሩን ብልጫውን በመውሰድ ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶቾን ያደረጉ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች በተወሰኑ አጋጣሚዎች በእንደ ሁለት ቅብብል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳጥን ለመግባት ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ያብስራ ተስፋዬ ከአማኑኤል ገብረሚካኤል የደረሰውን ኳስ ለመጠቀም ሲሞክር የሀዋሳ ከተማው ተጫዋች መድኃኔ ብርሀኔ በራሱ ግብ ላይ አሳርፎታል ። በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታው ሶስት ነጥብ እና ሶሰት ጎሎ ይዞ ወጥቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 47 በማድረስ መሪነቱን ሲያጠናክር ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 34 ነጥብ በመያዝ በግብ ከፍያ ተበልጦ ወደ 5ኛ ደረጃ ተንሸራቷል ።በ22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ( ባህርዳር ) በመጪው ግንቦት 1 ( ሰኞ ) ሀዋሳ ከተማ ሰበታ ከተማን ሲገጥም በዕለቱ ሌላኛው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል ።