በ17ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ 9 ሰዓት ላይ በጀመረው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ለረጅም ደቂቃዎች ሲመሩ ቢቆዩም 90ኛው ደቂቃ ላይ በተቆጠረባቸው ግብ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ለመጋራት ተገደዋል ።
ሀዋሳ ከተማዎች በ16ኛው ሳምንት ጅማ አባጅፋርን በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ዳግም ተፈራ ፤ አብዱልባሲጥ ከማል እና ተባረክ ሄፌሞን በማሳረፍ መሀመድ ሙንታሪ ፤ ዳንኤል ደርቤን እና መስፍን ታፈሰን ያሰለፉ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ድሬዳዋ ከተማን ሲረቱ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ቅያሪ ብቻ በማድረግ ምንይሉ ወንዱምን በስንታየሁ መንግስቱ ምትክ አሰልፈዋል ።በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ አዝማሚያዎች የታዩ ሲሆን ወደ ሳጥኑ አካባቢ የሚደርሱ ኳሶች ግን ወደ ግብነት አልያም ወደ ጥሩ ሙከራ ከመቀየር ይልቅ በተጋጣሚ ተከላካዮች የሚመለሱ ነበሩ ።
በአጋማሹ የነበረው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ 25ኛው ደቂቃ ላይ በወላይታ ድቻ በኩል የተመለከትነው ሲሆን ያሬድ ዳዊት ከማዕዘን ያሻማውን ኳር አንተነህ ጉግሳ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ቢልከውም መድኃኔ ብርሀኔ ከግቡ አፋፍ ላይ አውጥቶታል ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል 30ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ በየነ በወላይታ ድቻ ተከላካዮች መካከል ለወንድማገኝ ሀይሉ ያደረሰው ኳስ በፅዮን መርዕድ መረብ ላይ አርፎ ሀዋሳ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል ። ከግቡ በኋላም በፈጣን ኳሶች ወደ ግብ ክልል አቅራቢያ መድረሳቸውን ቢቀጥሉም ሌላ ግብ ሳይታከል የመጀመሪያው አጋማሽ በሀዋሳ ከተማ 1 – 0 መሪነት ተጠናቋል።በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ወላይታ ድቻዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል በመድረስ በተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ለረጅም ደቂቃዎች የጣሩ ቢሆንም የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ኳሶቹን በመመለስ ግብ እንዳይስተናገድባቸው ማድረግ የቻሉ ሲሆን የሚመለሱትንም ኳሶች በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል በማድረስ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በአጋማሹ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ ያደረጉት ሀይቆቹ ሲሆኑ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ በኤፍሬም አሻሞ በኩል አልፎ ብሩክ በየነ በግንባር ወደ ግብ ቢልከውን በግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ ተይዞበታል።
ቀጣዩ የግብ ሙከራ ከ23 ደቂቃዎች በኋላ የተደረገ ሲሆን ያሬድ ዳዊት ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከው ኳሶ በግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ በቀላሉ ተይዟል ። በበ79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በሀዋሳ ከተማ በኩል መድኅኔ ብርሀኔ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ለተባረክ ቀንሶለት የነበረ ቢሆነም ተባረክ ያገኘውን ኳስ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በ81ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው እንድሪስ ሰይድ በአዲስአለም ላይ በሰራው ጥፋት የዕለቱ የመሀል ዳኛ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብቶታል ።ወላይታ ድቻዎች በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በቃልኪዳን ዘላለም ያደረጉት ድንቅ የግብ ሙከራ በመሀመድ ሙንታሪ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የማዕዘን ምቱም በአዲስ ህንፃ ሲሻገር ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ በግንባር በመግጨት በሀዋሳ ከተማ መረብ ላይ አሳርፎታል ።
ወላይታ ድቻም ከመሸነፍ ተርፎ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል ።ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ክለቦች ነጥባቸውን በአንድ አንድ ከፍ ያደረጉ ሲሆን ወላይታ ድቻ 32 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በ31 ነጥብ በነበሩበት የ2ኛ እና 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ቀጥለዋል ።
በ18ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ረቡዕ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሮዱዋ ደርቢ ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን ሲገጥም በማግስቱ ቀን 9 ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ወላይታ ድቻ አዳማ ከተማን ይገጥማል ።