የፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲጀመሩ በመጀመሪያው ጨዋታ ሁለቱን የኦሮሚያ ክልል ክለቦች ያገናኘ ሲሆን በጨዋታውም በፋሲል ተካልኝ የሚመራው አዳማ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል ።
ሁለቱም ክለቦች በመጀመሪያው አሰላለፍ ከመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታቸው የተወሰኑ ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ጅማ አባጅፋር አራት እንዲሁም አዳማ ከተማ ሶስት ቅያሪዎችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል ።
ጨዋታው በመጀመሪያ ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ፊት ሄደው ግብ ለማስቆጠር ጥሩ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴዎችን ያደረጉ ሲሆን በ4ኛው ደቂቃ ላይ ወጣቱ አጥቂ መሀመድኑር ናስር ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ነፃ ሆኖ አግኝቶት ወደ ግብ ቢሞክረውም ምቱ ጠንካራ ባለመሆኑ የአዳማ ከተማው የግብ ዘብ ሴኩባ ካማራ በቀላሉ ሊይዘው ችሏል ። በአዳማ ከተማ በኩል የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት በ9ኛው ደቂቃ በአሜ መሀመድ አማካይነት ሲሆን የተመታውን ኳስ የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ ታምራት ዳኜ ሊያወጣው ችሏል ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የአስራዎቹ ደቂቃ መጨረሻ አካባቢ በላይ አባይነህ በአብዲሳ ጀማል ላይ ጥፋት በመስራቱ አዳማ ከተማዎች የቅጣት ምት አገኙ ። የቅጣት ምቱን ከዚህ ቀደም በጥሩ የቅጣት ምት መቺነቱ የሚታወቀው አምበሉ ዳዋ ሆቴሳ መቶት 20ኛው ደቂቃ ላይ ግብ መስቆጠር ችለዋል ።
ጅማ አባጅፋሮች ከግቧ መቆጠር በኋላ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ወደ ፊት ለመሄድ ጥረቶች ያደረጉ ሲሆን በተለይም 27ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ ከጎሉ አቅራቢያ ሆኖ ወደ ግብ መቶት ግብ ጠባቂው ተፍቶት በድጋሚ ዱላ ሙላቱ ሞክሮት የግቡ ቋሚ የመለሳት ኳስ ለአሸናፊ በቀለ ቡድን አስቆጪ ነበረች ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም በአዳማ ከተማ መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ 47ኛ ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጣሪው ዳዋ ሆቴሳ ከአሜ መሀመድ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቢሞክራትም በታምራት ዳኜ ሊመለስ ችሏል ።
በጨዋታው ግብ ከማስቆጠሩም ባሻገር ጥሩ ብቃትን ሲያሳይ የነበረው ዳዋ 65ኛ ደቂቃ ላይ ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢሞክረውም በድጋሚ ግብ ጠባቂው አድኖበታል ። በ71ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ 20 ቁጥር አባይ በላይነህ ከርቀት የመታው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በግብ ጠባቂው ሴኮባ ካማራ አማካኝነት ለጥቂት ግብ ሳይሆን ቀርቷል ።
በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ በተለይም የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ የነበረው ጅማ አባጅፋር ኳሱን ከመረብ የሚያገናኝለት ተጫዋች ማግኘት አልቻለም ። የጨዋታው የመጨረሻ ውጤትም ጅማ አባጅፋር 0 አዳማ ከተማ 1 በመሆን ተጠናቋል ። ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ በ4 ነጥብ በጊዜያዊነት የሊጉ የደረጃ አናት መቆናጠጥ ችሏል ።