የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሀዋሳ ፣ በድሬዳዋ እና በአዳማ ከተማ ከተደረገ በኋላ ከ22ኛ ሳምንት ጀምሮ በባህርዳር ከተማ የሚያደርገውን ቆይታ ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ በተደረገው የጅማ አባጅፋር እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ጅማሮውን ማድረግ ችሏል ። በጨዋታውም በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር ከ1 – 0 መመራት ተነስቶ በአስጨናቂ ፀጋዬ እና እዮብ አለማየሁ ግቦች 2 – 1 አሸንፏል ።ጅማ አባጅፋሮች በ21ኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ሲረቱ ከተጠቀሙት ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ሽመልስ ተገኝን እና ሱራፌል ዐወልን በወንደማገኝ ማርቆስ እና መሀመድኑር ናስር ምትክ ሲያሰልፉ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ በወልቂጤ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን ኡቸና ማርቲንን ፤ ሙና በቀለን ፤ ሀቢብ ከማልን እና ፍቃዱ መኮንንን በበርናንድ ኦቼንጌ ፤ አሸናፊ ፊዳ ፤ በላይ ገዛኸኝ እና ኤሪክ ካፓይቶ ተክተው ገብተዋል ።
ረፋድ 4:00 ላይ በተጀመረው ጨዋታ ጅማ አባጅፋሮች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የጀመሩት ሲሆን አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ በርከት ብለው በመገኘት የጅማ አባጅፋርን የኳስ ፍሰት በማቋረጥ በረጃጅም ኳሶች እና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ጅማ አባጅፋር የግብ ክልል ለመድረስ የሞከሩበት ነበር ።
በግብ ሙከራዎች ያልታጀበው ጨዋታ ከውሀ እረፍት መልስ የመጀመሪያውን ግብ አስመልክቶናል ። 29ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ኤልያስ ከበላይ ገዛኸኝ በረጅም የተላከለትን ኳስ ከተከላዮች ጀርባ በመሮጥ ከሳጥኑ የግራ አቅጣጫ አካባቢ ሆኖ ወደ ግብ የላከውን ኳስ በአላዛር ማርቆስ መረብ ላይ አሳርፏል ።ጅማ አባጅፋሮች በመመራት ብዙም ሳይቆዩ መልስ መስጠት የቻሉ ሲሆን ግብ ካስተናገዱ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ አርባምንጭ ከተማዎች ከግብ ክልል ለማራቅ የተቸገሩትን ኳስ ተካልኝ ደጀኔ ከሳጥኑ ለማውጣት ሲሞክር አስጨናቂ ፀጋዬ ተደርቦ ከመረብ ላይ አሳርፎታል ።34ኛው ደቂቃ ላይ አድናን ረሻድ ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ለዳዊት ፍቃዱ ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ሳይደርስበት ቀረ እንጂ ለጅማ አባጅፋር ሁለተኛ ግብ ሊሆን ይችል ነበር ።
ከግቡ በኋላ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ከተከላካይዮች ጀርባ ክፍተቶችን በመፍጠር ለፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው ኳሶችን ለማድረስ ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ። በጅማ አባጅፋር በኩል በተወሰነ መልኩ ከአዞዎቹ የሚነጠቁ ኳሶችን ወደ ፊት ይዘው ለመድረስ የሞከሩበት ሲሆን በተለይም በ43ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ እና ሱራፌል ዐወል ያደረጉት ድንቅ ቅብብል ወደ ሳጥን ደርሶ ሱራፌል በመጨረሻም በግራ እግሩ አክርሮ ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያው አጋማሽም በ1 – 1 ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ወደ ፊት በመንቀሳቀስ የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ቀስ በቀስ በጅማ አባጅፋሮች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ወደ ሜዳ ክፍላቸው ለማፈግፈግ ቢገደዱም የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጃጅም በመጣል በተለይም በፍቃዱ መኮንን አማካኝነት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።በአጋማሹ የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚም በ48ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው ፍቃዱ መኮንን የተደረገ ሲሆን ፍቃዱ በረጅም የደረሰውን ኳስ ከፊቱ የነበረውን ብቸኛ ተከላካይ ያብስራ ሙሉጌታን አልፎ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ፍቃዱ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የመታው ኳስ ለጥቂት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ጅማ አባጅፋሮች ምንም እንኳን ኳሱን ይዘው በመጫወት በተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢኖራቸውም የአርባምንጭ ከተማን የመከላከል መስመር ሰብረው የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል ።
የጨዋታው የኳስ ፍሰት በአብዛኛው በመሀል የሜዳው ክፍል ላይ በሆነበት እና በሁለቱም በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ደከም ባሉበት ጊዜ ጅማ አባጅፋሮች ከመመራት ወደ መሪነት የመጡበትን ግብ አስቆጥረዋል ።በ76ኛው ደቂቃ ላይ እዩብ አለማየሁ በቀኝ አቅጣጫ የደረሰውን ረጅም ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት ግብ ጠባቂውን ሳምሶን አሰፋን አልፎ ከፊቱ ሁለት ተከላካዮች የነበሩ ቢሆንም እዮብ በተከላካዮቹ መካከል ወደ ግብ የላከው ኳስ ከመረብ ላይ አርፎ የጨዋታውን ውጤት ወደ 2 – 1 ቀይሮታል።
አዞዎቹ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ላይ በተሻለ ወደ ጅማ አባጅፋር የሜዳ ክፍል በማለፍ ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ይህ ነው ሊባል የሚችል ጠንካራ የግብ ሙከራን ለማድረግ ግን አልቻሉም ።
በ84ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ መኮንን በተከላካዮች ተከቦ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታውን ኳስ አላዛር ማርቆስ በቀላሉ አድኖታል ።በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በጅማ አባጅፋር በኩል ሶስተኛውን ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የነበረ ሲሆን ሱራፌሌ ዐወል ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር ምንም እንኳን ደረጃው አሁንም 15ኛ ቢሆንም ነጥቡን 19 ማድረስ የቻለ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ በ26 ነጥብ በነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ የሚቆይ ይሆናል።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 3 ( ረቡዕ ) ቀትር 7 ሰዓት ላይ ጅማ አባጅፋር ሰበታ ከተማን ሲገጥም አርባምንጭ ከተማ ደግሞ 10 ሰዓት ላይ ከአዳማ ከተማ ጨዋታውን ያደርጋል ።