በስድስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ አባጅፋርን የገጠመው ባህርዳር ከተማ በአሊ ሱሌይማን ሁለት ግቦች አሸንፎ ወጥቷል ።
ጅማ አባጅፋሮች በአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ከተጠቀመው ምርጥ 11 አራች ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን ሽመልስ ተገኝ ፤ አላዛር ሳሙኤል ፤ አሳሪ አልመሀዲንን እና መሀመድኑር ናስርን እንዲሁም ባህርዳር ከተማ በበኩሉ በረከት ጥጋቡን እና ኦሴ ማውሊን ወደ ቋሚ አሰላለፍ መልሰው ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ከሽንፈት የመጡ እንደመሆናቸው ይህን ጨዋታ አሸንፈው ለመውጣት በሜዳ ላይ ብርቱ ትግል አድርገዋል ። በሁለቱም በኩል ከፍተኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየተበት ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በግብ ሙከራ ግን የታጀበ አልነበረም ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው 18ኛ ደቂቃ ላይ ባህርዳር ከተማ በአሊ ሱሌይማን አማካኝነት የመጀመሪያውን ግብ አስቆጠሩ ። አማካዩ አለልኝ አዘነ በግራ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ለአሊ ሱሌይማን አቀብሎት አሊ ቀጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮታል ።
ጅማ አባጅፋሮች ኳሱን ተቆጣጥረው የመጫወት ዝንባሌን ቢያሳዩም ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ግን የተሳካ አልነበረም ። በአንፃሩ ባህርዳር ከተማዎች በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ያደርጓቸው የነበሩ ጥረቶች የጅማ አባጅፋር የተከላካይ መስመርን የፈተኑ ነበሩ ። 28ኛው ደቂቃ ላይ ኦሴይ ማውሉ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ተመልሷል ። በተመሳሳይ 38ኛ ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው አላዛር ተመልሷል ።
ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል በመጀመሪያ አጋማሽ እንደነበረው በጥሩ ፉክክር ነቀጠለ ነበር ። ጨዋታውን እየመሩ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ 50ኛ ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ግብ አስቆጠሩ ። አብዱልከሪም ኒኪማ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ኡሊ ሱሌይማን ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ቻለ ።
በቀሩት ደቂቃዎች ጅማ አባጅፋሮች በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም በሶስተኛው የማጥቃት ዞን ሲገቡ የነበራቸው አጠቃቀም ደካማነት ግብ እንዳያስቆጥሩ አድርጓቸዋል ። ይባሱንም ባህርዳር ከተማዎች በፈጣን አጨዋወት ወደ ፋት በመሄድ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። በተለይም በፍፁም አለሙ አማካኝነት የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች መምከናቸው የጣና ሞገዶቹ መሪነታቸውን እንዳያሰፉ አድርጓቸዋል ።
በጨዋታው 83ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በላይ አባይነህ በግንባሩ ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
ውጤቱን ተከትሎም አሸናፊው ባህርዳር ከተማ ነጥቡን ወደ 10 ሲያሳድግ እስካሁን ምንም ማሸነፍ ያልቻለው ጅማ አባጅፋር ያለምንም ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል ።