በ20ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ተገናኝተው 1 – 1 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል ።
ጅማ አባጅፋሮች በ19ኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከነማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን አድርገው የገቡ ሲሆን ዳዊት እስጢፋኖስን እና ቦና አሊን በማሳረፍ ዳዊት ፍቃዱን እና በላይ ዓባይነህን ሲያሰልፉ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በሳምንቱ በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻን ሲረቱ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ሀይሌ ገብረትንሣኤን በስዩም ተስፋዬ ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምር አድርገዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ ለመጫወት ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
በ11ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድኑር ናስር በቀኝ መስመር አቅጣጫ ላይ የተሰነጠቀለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የነበረ ቢሆንም ወደ ግብ የላከው ኳስ በበረከት አማረ ተመልሶ ወቷል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳሽ ቁጥጥር ብልጫውን ለመውሰድ በነበረው ፉክክር የተሻለ መሆን የቻሉ ሲሆን የጅማ አባጅፋርን የመከላከል መስመር ግን አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ። በጨዋታው የነበረው ኢላማውን የጠበቀ የመጀመሪያ ሙከራቸውም በ20ኛ ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን ቴዎድሮስ በቀለ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ በአላዛር ማርቆስ ተመልሷል ።በቀሪዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ላይ ጅማ አባጅፋሮች የተሻለ ወደ ፊት አልፈው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ነበር ። ቡናማዎቹ በተወሰደባቸው ብልጫ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፈሰል ለመድረስ በተቸገሩባቸው ደቂቃዎች ላይ 40ኛው ደቂቃ ሲደርስ ሮቤል ተክለሚካኤል ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ።
- ማሰታውቂያ -
የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ምንም ግብ ተጠናቀቀ ።
የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ለቡናማዎቹ ባማረ ሁኔታ የጀመረ ነበር ። ሮቤል ተክለሚካኤል ለእንዳለ ደባልቄ የደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ የላከው ኳስ ከመረብ ላይ አርፏል ።ከግቡ በኋላ ጅማ አባጅፋሮች በተሻለ በመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ። 53ኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ፀጋዬ ከርቀት ወደ ግብ የላከው ኳስ ከግቡ አናት በላይ ወጥቷል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም በላይ ዓባይነህ ከአስራት ቱንጆ የነጠቀውን ኳስ መስዑድ መሀመድ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት በረከት አማረ መልሶታል ።
በ65ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባጅፋሩ 7 ቁጥር ለባሽ እዮብ አለማየሁ በሳጥኑ ጫፍ ላይ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በበረከት አማረ መረብ ላይ አርፎ የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 – 1 ቀይሮታል ።ወደ አቻ የተመለሰው ጨዋታ በምርጥ የሜዳ ላይ ፉክክር ቀጥሎ ለአይን ሳቢ እንቅስቃሴዎችን አሳይቷል ። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በ78ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ አላዛር ማርቆስን አልፎ የነበረ ቢሆንም የግቡ አግዳሚ ሲመልሰው ገዛኸኝ ደሳለኝ ኳሱን አግኝቶ ወደ በድጋሚ ወደ ግብ የላከው ኳስ በተከላካዩ ተመልሶ ወጥቷል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በ1 – 1 ውጤት ተፈፅሟል ።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥባቸውን 13 እና 28 ማድረስ ቢችሉም በደረጃቸው ላይ ለውጥ ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል ።በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው አርብ ቀን 9 ሰዓት ላይ ጅማ አባጅፋር ባህርዳር ከተማን ሲገጥም ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ምሽት 12 ሰዓት ላይ መከላከያን ይገጥማል ።