በ18ኛው ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የጅማ አባጅፋር እና የፋሲል ከተማ ጨዋታ አሰልጣኛቸውን ካሰናበቱ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ባደረጉት በፋሲል ከተማዎች የ2 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ጅማ አባጅፋሮች በ17ኛው ሳምንት በአዳማ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ቅያሪዎትን በማድረግ ሙሴ ከበላን እና ሱራፌል አወልን በእያሱ ለገሰ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ ሲያሰልፉ ፋሲል ከተማዎች ደግሞ በሳምንቱ በወልቂጤ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ለውጦቾን ያደረጉ ሲሆን በአስቻለው ታመነ ፣ ሀብታሙ ተከስተ እና ሱራፌል ዳኛቸው ምትክ ከድር ኩሊባሊን ፣ ይሁን እንደሻው እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ተክተው ገብተዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲል ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ በመሆን መጀመር የቻሉ ሲሆን የግብ ዕድሎችንም በመፍጠር ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ለመንቀሳቀስ ችለው ነበር ። በአንፃሩ ጅማ አባጅፋሮች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በኳስ ቁጥጥሩ ከፋሲል ከተማ ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማሳየት የፋሲልን የኋላ ክፍል ለመፈተን ሞክረዋል ።
በአጋማሹ የታየው የመጀመሪያ ሙከራ 25ኛ ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ የተመዘገበ ሲሆን በቀኝ መስመር አቅጣጫ ገብቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በግብ ጠባቂዎ አላዛር ማርቆስ ተመልሷል ። ከግብ ሙከራዎች ርቆ የቆየው ጨዋታ 38ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ እና መረብ ተዋህዶበታል ።የጅማ አባጅፋሩ ተጫዋች ሙሴ ከበላ ከግራ መስመር ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ መሀመድኑር ናስር በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል ። ከግቡ በኋላ ፋሲል ከተማዎች አጋማሹ ሳይጠናቀቅ የአቻነቱን ግብ ለማስቆጠር በቀሩት ደቂቃዎች ጥረቶችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል ።ሁለተኛውን አጋማሽ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት የጀመሩርተ አፄዎቹ የተሻለ ወደ ግብ መቅረብ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ52ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። በሳጥን ውስጥ የነበረው በረከት ደስታ ከሳጥኑ ውጪ ለነበረው ይሁን እንደሻው ያቀበለወሰን ኳስ ይሁን በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት በአላዛር መረብ ላይ አስቆጠረ ።በግቡ የተነቃቁት ፋሲል ከተማዎች በጅማ አባጅፋር ተከላካዮች ላይ ጫና ማሳደራቸውን አጠናክረው በመቀጠል ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። በ57ኛው ደቂቃ ላይ ሽመከሰት ከሳጠሰን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው አላዛር ሲመለስ ከአንድ ደቂቃ በኋላም በድጋሚ ከሱራፌል ዳኛቸው ወደ ግብ የተላከው ኳስ በድጋሚ በአላዛር ግብ ከመሆን ድኗል ።ጅማ አባጅፋሮች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ፊት ለመድረስ እና ዳግም መሪ ለመሆን ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል ። በተለይም በ79ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ የፋሲል ከተማ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ መቀየር ሳይችል ቀርቷል ።
ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሙሴ ከበላ በያሬድ ባየህ ላይ በሰራው ጥፋት የቀይ ካርድ በመመልከት ከሜዳ ወጣ ። ይህም ጅማ አባጅፋሮችን ቀጣዮቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት አስገደዳቸው ።
- ማሰታውቂያ -
መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው ሳጥን ውሰጥ ለነበረው ፍቃዱ አለሙ የደረሰው ኳስ ነፃ ለነበረው ኦኪኪ አፎላቢ ደርሶ ኦኪኪ በግሩም አጨራረስ የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ በማስቆጠር አፄዎቹን አሸናፊ ማድረግ ቻለ ።ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከተማ ነጥቡን 30 ማድረስ ቢችልም በነበረበት 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ጅማ አባጅፋርም በነበረበት 12 ነጥብ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማ አባጅፋር በመጪው ሰኞ ቀን 9 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥሙ በማግስቱ ምሽት 12 ሰዓት ላይ ፋሲል ከተማ አዲስ አበባ ከተማን ይገጥማል ።