በ16ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ አባጅፋርን ከሀዋሳ ከተማ አገናኝቶ ብሩክ በየነ እና ተባረክ ሔፋሞ ባስቆጠሯቸው ግቦች ሀይቆቹ ማሸነፍ ችለዋል ።
ጅማ አባጅፋሮች በ15ኛው ሳምንት ከመከላከያ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን በማድረግ ተስፋዬ መላኩን ፣ ሙሴ ከበላን እና በላይ ዓባይነህን ወደ አሰላለፍ ሲመልሱ በሀዋሳ ከተማ በኩል በሳምንቱ ከአዳማ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ በተመሳሳይ ሶስት ለውጦችን በማድረግ ግብ ጠባቂውን ዳግም ተፈራ ፣ ላውረንስ ላርቴን እና ተባረክ ሔፋሞን በጨዋታው ላይ ማሰለፍ ችለዋል ።ጨዋታው ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴዎች የታጀበ ነበር ። ጅማ አባጅፋሮች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን በመውሰድ የሀዋሳ ከተማን የኋላ መስመር ለማስከፈት ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ የሚነጠቁ ኳሶችን በፈጣን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመውሰድ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በጨዋታው 15ኛ ደቂቃ ላይም በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ከላይ በተጠቀሰው አጨዋወት ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ በወንድማገኝ ሀይሉ ለግብ አመቻቺነት እና በብሩክ በየነ ግሩም አጨራረስ እና መረብን አገናኝተዋል ።ግብ ካስተናገዱም በኋላ ኳሱን ይዘው በመጫወት የበላይ የነበሩች ጅማ አባጅፋሮች የሀዋሳ ከተማን ተከላካይ ለማስከፈት ተቸግረው ቆይተዋል ። በአጋማሹም 19ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በእዮቦ በኩክ አልፎ ያገኘው ሙሴ ከበላ ለግቡ ቅርብ ሆኖ ካመከነው ሷስ ውጪ ሌላ ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ።
በሁለተኛው አጋማሽም ጅማ አባጅፋሮች በኳስ ቁጥጥሩ የነበራቸወሰን የበላይነት በማስቀጠል እና ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለለ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩበት ነበር ። በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግቦችን ለማከል ሲጥሩ ተስተውሏል ።
በአጋማሹ የነበረው የመጀመሪያው የግብ ሙከራ በ47ኛው ደቂቃ ላይ በጅማ አባጅፋር በኩል የታየ ሲሆን ዳዊት ከመሀመድኑር የደረሰውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ አምክኖታል ።
- ማሰታውቂያ -
ጨዋታው በጥሩ ፍሰት የቀጠለ ሲሆን 65ኛው ደቂቃ ግን ለሀዋሳ ከተማዎች መሪነታቸወን ወደ ሁለት ያሳደጉበት ለጅማ አባጅፋሮች ደግሞ ቅስም ሰባሪ ግብ የተቆጠረበት ነበር ። የግቡ ባለቤቶ ተባረክ ሔፋሞ ሲሆን መድኃኔ ብርሀኔ ከግራ መስመር ያሻገረለትን በአላዛር ማርቆስ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ።ጅማ አባጅፋሮች አሁንም ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ቢቀጥሉም ግብ ጠባቂውን ዳግም ተፈራን የፈተነ ከባድ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ነበር ። በሀዋሳ ከተማ በኩል በፈጣን መልሶ ማጥቃት በፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው ተጨማሪ ግብ ለማከል ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ። በመጨረሻም ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ የ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 30 በማድረስ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ጅሣ አባጅፋር በበኩሉ በነበረበት 11 ነጥብ እና 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ጅማ አባጅፋር በመጪው አርብ ምሽት 12 ሰዓት ላይ አዳማ ከተማን ሲገጥም ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በዕለቱ ቀን 9 ሰዓች ላይ ወላይታ ድቻን የሚገጥም ይሆናል ።