ጅማ አባጅፋር በውድድር አመቱ በዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ስምንት ሽንፍት እና አንድ የአቻ ውጤት ካስመዘገበ በኋላ በአስረኛው ሳምንት ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማን በማሸነፍ ከድል ጋር ታርቋል ።
ጅማ አባጅፋር በዘጠነኛው ሳምንት ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ 11 ዱላ ሙላቱን በማሳረፍ ዳዊት ፍቃዱን ያሰለፉ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ዋኬኔ አዱኛ ፤ ብሩክ ግርማ ፤ ኤልያስ አህመድ ፤ ቻርለስ ሪባኑ እና ያሬድ ሀሰንን በዳንኤል ተሾመ ፤ ሳሙኤል አስፈሪ ሳሙኤል ተስፋዬ ፤ ብዙአየሁ ሰይፉ እና ሙሉቀን አዲሱ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጅማ አባጅፋሮች በተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር ። መገር ግን በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ግብ በመድረስ ብልጫ ቢያሳዩም የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ነበር ። አዲስ አበባ ከተማዎች ቀስበቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በፈጣን እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገው በ11ኛው ደቂቃ ላይ ነበር ። ፍፁም ጥላሁን ከመስመር ከእንዳለ ከበደ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በግጓግ ጠባቂው አልዓዛር ማርቆስ ተመልሶበታል ። ከሙከራው በኋላ በሁለቱም ክለቦች በኩል በተለይም በመስመር በኩል የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የቻሉበት ነበር ። ነገር ግን ያን ያህል ለአይን የሚስብ የግብ ሙከራ ሳይደረግ ነበር የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው ።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት ፉክክር የተደረገ ነበር ። በጅማ አባጅፋርም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የመድረስ አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም ተከላካዮችንም ሆነ ግብ ጠባቂዎችን የፈተኑ የግብ ሙከራዎች ሳይደረጉ ኳሶች ይበላሹባቸው ነበር ።
በአጋማሹ ኢላማውን የጠበቀ የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው ተቀይሮ በገባው በላይ አባይነህ አማካኝነት ሲሆን ተጫዋቹ 61ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ተመልሷል ። ጨዋታው በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በተመጣጣኝ ፉክክር ቢቀጥልም በግብ ሙከራዎች ሊታጀብ አልቻለም ።
በ78ኛው ደቂቃ ላይ ግን አማካዩ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ምት ግሩም ግብ በማስቆጠር ጅማ አባጅፋርን መሪ አደረገ ። ከግቡ በኋላ ቀድሞ ከነበረው ግለት ጨምሮ የቀጠለው ጨዋታ በሁለቱም በኩም ጠንከር ያሉ የማጥቀታ ሂደቶች እና የግብ ዕድሎች ቢፈጠሩም ሌላ ኳስን ከመረብ ያገናኘ ተጫዋች አልነበረም ። ጨዋታውም በጅማ አባጅፋር አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
በውድድር አመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳኩት ጅማ አባጅፋሮች ነጥባቸውን 4 ማድረስ ቢችሉም በደረጃ ሰንጠረዡ ግን ለውጥ ማድረግ አልቻሉም በተመሳሳይ ተሸናፊው አዲስ አበባ ከተማም የደረጀሠ ለውጥ ሳያደርግ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።