በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረባቸው ግብ ሲመሩ የቆዩት ሀዋሳ ከተማዎች ከዕረፍት መልስ ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች መከላከያን 2 – 1 መርታት ችለዋል ።
መከላከያ በ28ኛው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራተ ለውጦችን በማድረግ በክሌመንት ቦዬ ፤ ዳዊት ማሞ ፤ አሌክስ ተሰማ እና ቢንያም በላይ ምትክ ሙሴ ገብረኪዳን ፤ ኢብራሂም ሁሴን ፤ ገናናው ረጋሳ እና ባድራ ናቢ ሲላን ሲያሰልፉ በሳምንቱ በፋሲል ከነማ የተረቱት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በጨዋታው ከተጠቀሙት ምርጥ 11 አምስት ለውጦችን በማድረግ ምንተስኖት ጊንቦ ፤ አዲስአለም ተስፋዬ ፤ ሄኖክ ድልቢ ፤ ዮሀንስ ሴጌቦ እና መስፍን ታፈሰን በቋሚ አሰላለፍ በማካተት መሀመድ ሙንታሪ ፤ ካሎጂ ሞንዲያ ፤ ዳንኤል ደርቤ ፤ በቃሉ ገነነ እና ኤፍሬም አሻሞን በተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጠዋል ።
በፈጣን እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ መከላከያዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገው ነበር። በተለይም በመስመሮች በኩል የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ሙከራዎችን በማደረጉ ረገድ ደካማ ጊዜ ነበር ያሳለፉት ።
- ማሰታውቂያ -
በሀዋሳ ከተማ በኩል በፈጣን ሽግግሮች ወደ መከላከያ የግብ ክልል የመድረስ ፍላጎት ቢያሳዩም በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ላይ ሲገቡ የነበራቸው የኳስ ቅብብል በቀላሉ በመከላከያ ተጫዋቾች እግር ስር ይገባ ነበር ።
በ17ኛው ደቂቃ ላይ በሀዋሳ ከተማ በኩል ወንድማገኝ ሀይሉ በቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ መስፍን ታፈሰ ሳይጠቀመበት ቀርቷል ።
በመከላከያ በኩል 36ኛው ደቂቃ ላይ ተሾመ በላቸው በቀኝ መስመር ይዞ የሄደውን ኳስ ለምንተስኖት አቀብሎት ከሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ላይ ምንተስኖት አዳነ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ኳሱ ኢላማውን ባለመጠበቁ ሳይሳካ ቀርቷል ።
መደበኛው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ጦሩ ቀዳሚ መሆን የቻለበትን ግብ አግኝቷል ። ግሩም ሀጎስ ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ተሾመ በላቸው ከሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ጀርባ ገብቶ ኳሱን ከመረብ ላይ አሳርፎታል ።
የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ መከላከያዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመሩት ነበር ። በ47ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ በአመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን በማድረግ ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ምንተስኖት ኳሱን ለመቆጣጠር ሲሞክር ከእጁ ላይ አምልጦት ሊቆጠር የነበረ ቢሆንም ለጥቂት ግብ ከመሆን አድኖታል ። ከሶሰት ደቂቃዎች በኋላም አዲሱ አቱላ ከርቀት ያደረገውን ሙከራ ምንተስኖት መያዝ ችሏል ።
ጨዋታው 58ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ለሀዋሳ ከተማ ግቦችን እያስቆጠረ ያለው ብሩክ በየነ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ሀይቆቹን አቻ አድርጓል ።
ከግቡ መቆጠር በኋላም መከላከያዎች በመስመር ባደሉ እንቅስቃሴዎቻቸው ዳግም መሪ ለመሆን ጥረቶችን ማድረግ ችለው ነበር ። በ68ኛው ደቂቃ ላይ ምንተስኖት አዳነ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ጠንካራ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሞክሼው ግብ ጠባቂ ግብ እንዳይሆን ማድረግ ችሏል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሀይቆቹ ከመመራት ወደ መሪነት የተሸጋገሩበትን ግብ አግኝተዋል ። ወንድማገኝ ሀይሉ ከብሩክ በየነ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ሳጥን ለመግባት ያደረገው ጥረት የመከላከያ ተከላካዮች ስህትት ተጨምሮበት በ2013 የሊጉ ኮከብ ወጣት ተጫዋች ወንደማገኝ ሀይሉ ግብ አስቆጥሯል ።
መከላከያዎቾ ግቡ በተቆጠረ በሰከንዶች ልዩነት መልስ ለመስጥት ተቃርበው ነበር ። እስራኤል እሸተለ በረጅም የደረሰውን ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ኳሱ በመርዘሙ ሳይሳካ ቀርቷል ።
በመጨረሻቹ ደቂቃዎች ላይ መከላከያዎች ግብ አስቆጥረው ከጨዋታው ቢያንስ አንድ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 45 አድርሶ በነበረበት 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥል መከላከያ በበኩሉ በ34 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል ።
በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 24 ( ሀሙሰ ) 7:00 ላይ መከላከያ ጅማ አባጅፋርን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ረፋድ 4:00 ላይ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን ይገጥማል ። ( መርሀ ግብሮቹ የ29ኛ ሳምንት ውጤቶችን ተከትሎ ሊቀየሩ ይችላሉ )