በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የመከላከያ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል ።
በ14ኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ 3 ለ 2 የተረቱት መከላከያዎች በጨዋታው ተጠቅመውት ከነበረው አሰላለፍ ሶስት ለውጦችን በማድረግ የገቡ ሲሆን በቢንያም በላይ ፣ አዲሱ አቱላ እና ገናናው ረጋሳ ምትክ ቢንያም ላንቃሞ ፣ አቤል ነጋሽ እና ኢብራሂም ሁሴን ጨዋታውን እንዲጀምሩ ያደረጉ ሲሆን በተመሳሳይ ውጤት በወልቂጤ ከተማ 3 ለ 2 የተረቱት ጅማ አባጅፋሮች ደግሞ በጨዋታው ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ዱላ ሙላቱ እና አድናን ረሻድ በማስገባት አዛህሪ አልመሀዲ እና በላይ ዓባይነህን በተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጠዋል ።ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በማርሽ ባንድ በታጀበ ስነ ስርዓት የአድዋ ድል ጀግኖችን የማሰብ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን የአበባ ጉንጉን በክብር እንግዶች እና በጅማ አባጅፋር አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከተቀመጠ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ ጨዋታው ተጀምሯል ።
በእንቅስቃሴ ረገድ እምብዛም የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ያስመለከተ ሲሆን በሁለቱም በኩል አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳይደረግ ነበር አጋማሹ የተጠናቀቀው ።
መከላከያዎች የሚያገኟቸውን ኳሶች በመስመር ባሉ ተጫዋቾች በኩል አድርገው ወደ ግብ ክልል ኳሶችን ለማድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች በጅማ አባጅፋር ተከላካዮች በተደጋጋሚ ተመልሰዋል ። በጅማ አባጅፋር በኩል ደግሞ ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ መከላከያ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ከፊት መስመር ላይ የነበረባቸው የመናበብ ክፍተት በቀላሉ የመከላከያን የኋላ መስመር ሰብረው እንዳይገቡ አግዷቸዋል ።የሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ብዙም የተለየ አልነበረም ።
በመከላከያ በኩል ተቀይሮ የገባው ሰመረ ሀፍተይ በ46ኛው ደቂቃ ላይ ከኢማኑኤል ኦኩቱ ተቀብሎ ወደ ግብ የላከው ኳስ በቀላሉ በግብ ጠባቂው አላዛር ተይዟል ። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በጅማ አባጅፋር በኩል ለሳጥኑ በቅርብ ርቀት ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት በክሌመንት ቦዬ ግብ ከመሆን ድኗል ።መከላከያዎች ወደ ሳጥን በአየር በሚጣሉ ኳሶች አጥቂዎቻቸውን ለማግኘት ያደረጓቸው ሙከራዎች ውጤታማ ሊያደርጓቸው አልቻሉም ። በአንፃሩ በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ ለመድረስ የተቸገሩት ጅማ አባጅፋሮች ቀስ በቀስ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት በመውሰድ የመከላከያን ግብ ለመድፈር ጥረቶችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ63ኛ ደቂቃ ላይ አድናን ረሺድ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘ የቅጣት ምት በዳዊት እስጢፋኖስ ወደ ግብ ተሞክሮ ለጥቂት በመከላከያው ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ የማዕዘን ምት ሆኗል ። በዮሀንስ ሳህሌ የሚመሩት መከላከያዎች ምንም አይነት ግብ ጠባቂውን የፈተነ ኳስ ወደ ግብ ሳይልኩ ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ችለዋል ።መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ ያብስራ ተስፋዬ በብሩክ ሰሙ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 18 በማድረስ ወደ 11ኛ ከፍ ሲል ጅማ አባጅፋር ነጥቡን 11 ማድረስ ቢችልም የደረጃ ለውጥ ሳያደርግ በ15ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል ።
በ16ኛው ሳምንት ( አዳማ ከተማ ) መከላከያ አርባምንጭ ከተማን ጅማ አባጅፋር ደግሞ ሀዋሳ ከተማን የሚገጥሙ ይሆናል ።