የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ማሸነፍ ያልቻለውን አዲስ አበባ ከተማ እና በውድድር አመቱ አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበውን ሰበታ ከተማን አገናኝቶ በመዲናዋ ክለብ 5 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በ12ኛ ሳምንት ጨዋታ በሀድያ ሆሳዕና የተሸነፉት ሰበታ ከተማዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ስድስት ቅያሪዎችን በማድረግ ሰለሞን ደምሴን ፣ አለማየሁ ሙለታን ፣ ሃይለሚካኤል አደፍርስን ፣ ዘላለም ኢሳይያስን ፣ ፍፁም ገብረማርያምን ፣ ዘላለም ፍቅሬን በማሳረፍ ለዓለም ብርሀኑን ፣ ጌቱ ሀይለማርያምን ፣ ታፈሰ ሰርካን ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ፣ መሀመድ አበራን እና ዴሪክ ንሲባምቢን ወደ አሰላለፉ ያስገቡ ሲሆን በሳምንቱ በኢትዮጵያ ቡና የተሸነፉት አዲስ አበባ ከተማዎች በጨዋታው ከነበረው ቋሚ 11 አራት ለውጦችን በማድረግ ሮቤል ግርማን ፣ ዋለልኝ ገብሬን ፣ እንዳለ ከበደን እና ሪችሞንድ ኦዶንጎን በሳሙኤል ተስፋዬ ፣ ቢንያም ጌታቸው ፣ ኤልያስ አህመድ እና በየሺዋስ በለው ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ።
በጨዋታው አዲስ አበባ ከተማዎች በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ታጅበው ያገኟቸውን የግብ እድሎች በአግባቡ መጠቀም የቻሉበት ሲሆን በሰበታ ከተማ በኩል በሳምንቱ አዲስ አጥቂ ወደ ቡድኑ በመቀላቀል የቡድኑን የፊት መስመር ለማጠናከር ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ከነበረው የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያው ግብ የተቆጠረው በ13ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ግቡ ማስቆጠር የቻሉት ደግሞ አዲስ አበባ ከተማዎች ናቸው ። እንዳለ ከበደ ከመስመር ያሻገረው ኳስ በፍፁም ጥላሁን በኩክለ አልፋ በጋናዊው አጥቂ ሪችሞንድ ኦዶንጎ አማካኝነት በለዓለም ብርሀኑ መረብ ላይ አርፏል ። ከአስር ደቂቃዎች በኋላም በመዲናዋ ክለብ በኩል በቻርለስ ሪባኑ አቀባይነት እና ፍፁም ጥላሁን ጨራሽነት ሁለተኛ ግብ ተቆጥሯል ።
ሰበታ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ አንፃራዊ የበላይነት ቢኖራቸውም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው የግብ ዕድሎችን ከመፍጠር ረገድ በጣም ደካማ ነበሩ ። በ36ኛ ደቂቃ ላይም ሌላ ግብ አስተናግደዋል ።
ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረው ፍፁም ጥላሁን ከዋለልኝ ገብሬ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ በጨዋታው ለክለቡ ሶስተኛ ለራሱ ደግሞ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአዲስ አበባ ከተማ የ3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች በተመሳሳይ ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት ቢችሉም ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ደግሞ በፈጣን መልሶ ማጥቃት እና ከሚነጠቁ ኳሶች የግብ ዕድሎችን በመፍጠር መጠቀምም የቻሉበት ነበር ።
በ60ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን አዲሱ በሳጥን ውስጥ ሆኖ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የአዲስ አበባ ከተማን የግብ ልዩነት በማስፋት እና የሰበታ ከተማን በጨዋታው ላይ የነበረ ተስፋ አመናምኗል ። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ግን ዘካርያስ ፍቅሬ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል አስቆጥሮ የጨዋታውን ውጤት ወደ 4 ለ 1 ቀይሮታል ።
ነገር ግን ሰበታ ከተማዎች ግብ ካስቆጠሩ ብዙም ሳይቆዩ 70ኛ ደቂቃ ላይ ግብ ያስተናገዱ ሲሆን ግቡም የተቆጠረው በሮቤል ግርማ በቀጥታ ከቅጣት ምት ነበር ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ብሎ የቀጠለው ጨዋታ ሌላ ግብ ሳይቆጠርበት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ነጥቡን 14 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሰበታ ከተማ በተቆጠሩበት ግቦች ምክንያት ከ15ኛ ደረጃ ወደ 16ኛ ደረጃ ዝቅ ሊል ችሏል ።
በ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ ባህርዳር ከተማን አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ሲዳማ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል ።