በ30ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ አስቀድሞ መዉረዱን ያረጋገጠዉ ሰበታ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 1ለ0 በሆነ ዉጤት በማሸነፍ አመቱን በድል ደምድሟል።
በዉጤት ደረጃ ለሁለቱም ቡድኖች በተለይ ለሰበታ ከተማ እምብዛም ትርጉም ያልነበረዉ እና ቀን 10 ሰዓት ሲል የጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ አጀማመሩ የተቀዛቀዘ ነበር ፤ በአጨዋወት ረገድ አርባምንጭ ከተማዎች ተሽለዉ መንቀሳቀስ በቻሉበት በዚህ ጨዋታ በተደጋጋሚ ወደ ሰበታ የግብ ክልል ሲደርሱ የተስተዋለ ሲሆን በተለይ በፊት መስመር አጥቂዉ አህመድ ሁሴን እና በመስመር ተጫዋቹ አሸናፊ ኤልያስ አማካኝነት ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል።
በተቃራኒው በሰበታ ከተማዎች በኩል ደግሞ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ አብዝሀኛዉን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተቀዛቅዘዉ የተመለከትን ሲሆን በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸዉ ቡድን የተወሰኑ ሙከራዎችን ሲያስተናግዱ ለመመልከት ችለናል።
- ማሰታውቂያ -
ከዚህ በተጨማሪ ግን በተለይ ከ30ኛዉ ደቂቃ በኋላ የተወሰነ መነቃቃት አሳይተዉ በተቃራኒው በአጥቂያቸዉ ፍፁም ገ/ማርያም ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ እና ዱሬሳ ሺቤሳ አማካኝነት የአዞዎቹን የግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውሏል። ምንም እንኳን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የጨዋታ ሒደትን የተመለከተን ቢሆንም ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራም ሆነ ግብ ለመመልከት ግን ሁለተኛዉን አጋማሽ መጠበቅ የግድ ነበር።
ከዕረፍት መልስ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ የተመለከትነው በ66ኛዉ ደቂቃ ላይ ነበር ፤ በዚሁ ደቂቃ ላይም ከግራ በኩል የተገኘዉን ቅጣት ምት አሸናፊ ኤልያስ ቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ በግቡ አናት ለጥቂት የወጣበት ኳስ ለአዞዎቹ አስቆጭ ሙከሬ ነበረች ማለት ይቻላል።
ከዚች ሙከራ በኋላ ደግሞ የአርባምንጭ ከተማዉ ወጣቱ ተጫዋች አላዛር መምሩ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ዉስጥ ኳስ በዕጁ በመንካቱ ምክንያት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት የሰበታዉ አጥቂ ፍፁም ገ/ማርያም ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡ ሰበታ ከተማ አመቱን በድል እንዲደመድም አስችሏል።
ዉጤቱን ተከትሎም ሰበታ ከተማ በ25 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ በ40 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።