በ14ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ የተገናኙት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ባህርዳር ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩ ግቦች አንድ እኩል ውጤት ተጠናቋል ።
ሰበታ ከተማ በ13ኛው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በሰፊ ውጤት በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አራት ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን በለአለም ብርሃኑ ፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፣ ታፈሰ ሰርካ እና መሀመድ አበራ ምትክ ሰለሞን ደምሴ ፣ ሀይለሚካኤል አደፍርስ ፣ አንተነህ ናደውን እና ዱሬሳ ሹቢሳ ያሰለፉ ሲሆን በባህርዳር ከተማ በኩል ደግሞ ከድሬዳዋ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው አሰላለፍ ሁለት ቅያሪዎችን በማድረግ ፈቱዲን ጀማልን እና ፍቅረሚካኤል አለሙን በግርማ ዲሳሳ እና በረከት ጥጋቡ ተክተው ገብተዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች የባህርዳር ከተማን ከኋላ መስርቶ የመውጣት ፍላጎትን ጫና አሳድረው ኳሶችን በመንጠቅ እና በፈጣን ሽግግር ወደ ፊት ሄደው የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ለዚህም በመሀል ክፍል ላይ ያሉት ተጫዋቾች ጥሩ መሆን ቡድኑን በሚገባ ሲያግዘው ነበር ። በባህርዳር ከተማ በኩል ኳሱን ይዘው ለመጫወት ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤታማ ያልነበሩ ሲሆን የማጥቃት ሶስተኛው ዞን ለመግባት በአጅጉ የተቸገሩበት ነበር ።ሰበታ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ እስር ደቂቃዎች ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ኢላማቸውን መጠበቅ ሳይችሉ ቢቀሩም የባህርዳር ከተማ የተከላካይ መስመር ላይ የፈጠሩት ጫና በ14ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስገኝቶላቸዋል ። ግብ ጠባቂው ፋሲል ገብረሚካኤል ከመናፍ አወል የደረሰውን ኳስ ለሰለሞን ወዴሳ ለማቀበል ሲሞክር ኳሱ በማጠሩ የሰበታ ከተማው አዲስ ፈራሚ ኤሪክ ፓውል ኒስባምቢ ቀምቶ ለዱሬሳ ሹቢሳ ያቀበለውን ኳስ ዱሬሳ አጨራረሱን አሳምሮ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
የሞግሌዎቹ የመሀል ክፍል በመከላከሉም ሆነ የማጥቃት ሽግግሩን በማሳለጥ የነበራቸው ሚና ጥሩ የነበረ ሲሆን ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት የጣና ሞገዶቹ 21ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ በአሊ ሱሌማን አማካኝነት ከሳጥን ውጪ የተሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወቷል ። 33ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች የሜዳው መሀል ላይ ያገኙትን የቅጣት ምት በረከት ሳሙኤል ሳይጠበቅ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮት በፋሲል ገብረሚካኤል ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ።
በአጋማሹ በባህርዳር ከተማ በኩል የታየው ጥሩ የግብ ሙከራ 38ኛ ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን አምበሉ ፍቅረሚካኤል አለሙ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል ። የመጀመሪያው የጨዋታው አጋማሽም በሰበታ ከተማ መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሰበታ ከተማዎች በረጃጅም እና ከፈጣን መልሶ ማጥቃት በሚገኙ አጋጣሚዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ፊት መስመር ላይ የነበረው ድክመት ተጨማሪ ግብ ከማስቆጠር አግዷቸዋል ። በባህርዳር ከተማ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል መቅረብ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር የቻሉ ሲሆን ከእረፍት ከተመለሱ ከ13 ደቂቃዎች በኋላ በፍፁም አለሙ አቀባይነት እና በአሊ ሱሌማን ጨራሽነት የአቻነቱን ግብ አስቆጥረዋል ።በግቡ የተነቃቁ የሚመስሉት የጣና ሞገዶቹ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በፍፁም አለሙ እና ከሪም ኒኪማ አማካኝነት ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች በሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰለሞን ደምሴ ተይዘዋል ። ሰበታ ከተማዎች በፈጣን ሽግግሮቻቸው ወደ ባህር ዳር ከተማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ የቻሉባውን አጋጣሚዎች መፍጠራቸው ቢቀጥሉም አንድም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያደርጉ ነበር ጨዋታውን ያጠናቀቁት ። ምናልባትም 86ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ገብረማርያም ከሀይለሚካኤል አደፍርስ በረጅም የደረሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ አግኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ መናፍ አወል ከኋላ ደርሶ ያወጣበት ኳስ ለሞግሌዎቹ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር ። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ አራት ያህል የባከኑ ደቂቃዎች ከተጨመሩ በኋላ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።በጨዋታው አንድ አንድ ነጥብ ማግኘት የቻሉት ሁለቱም ክለቦችን በደረጃቸው ላይ ለውጥ ያላመጡ ሲሆን ባህርዳር ከተማ 6ኛ ላይ ሰበታ ከተማ ደግሞ 16ኛ ላይ ተቀምጠዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በ15ኛው ሳምንት ሰበታ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን የሚገጥሙ ይሆናል ።