በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና በሊጉ ግርጌ ላይ በሚገኘው በሰበታ ከተማ መካከል ተደርጎ አቡበከር ናስር እና ሮቤል ተክለሚካኤል ከርቀት ባስቆጠረው ድንቅ ግብ ቡናማዎቹ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በ18ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ በሰፊ ውጤት በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን አቤል ማሞን እና ተመስገን ገብረኪዳንን በበረከት አማረ እና ዊልያም ሰለሞን ተክተው ጨዋታውን የጀመሩ ሲሆን በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ መከላከያን ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ፍፁም ገብረማርያምን በቢስማርክ አፒያ ተክተው ገብተዋል ።በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሰበታ ከተማዎች በጥሩ መነቃቃት እና በተጋጣሚያቸው ላይ ጫና በመፍጠር የጀመሩት ነበር ። በዚህም በመልሶ ማጥቃት የተገኘን ኳስ ንስምባቢ ፍጥነት እና ጉልበቱን ተጠቅሞ በቀኝ መስመር በኩል ይዞ የሄደውን ኳስ ወደ ግብ ክልል አሻግሮት የነበረ ሲሆን ኳሱ የደረሰው ፍፁም ገብረማርያም ወደ ግብ የላከው ሙከራ ግን በግብ ጠባቂው በረከት አማረ ግብ ከመሆን ድኗል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች የተፈጠረባቸውን ጫና ቀስ በቀስ በመቀነስ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ኳሶችን ወደ ፊት ይዘው በማለፍ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት በ16ኛው ደቂቃ በመጀመሪያ ሙከራቸው ፍሬ አፍርቶላቸዋል ። በግራ መስመር በኩል የነበረው ዊልያም ሰለሞን ለሮቤል ተክለሚካኤል የሰጠው ኳስ ለአቡበከር ናስር የደረሰው ሲሆኖ የ2013 ዓ.ም የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ አቡበከር ከጨረቃው ላይ በቀጥታ መሬት ለመሬት ወደ ግብ የላከው ኳስ በምንተስኖት አሎ መረብ ላይ አርፏል ።ከግቡ በኋላ ቡናማዎቹ ኳሱን ከኋላ መስርተው ለመውጣት ቢሞክሩም ሰበታ ከተማዎች በፈጣን ኳሶች እና የተጋጣሚያቸው የኳስ ምስረታ ላይ ጫና በመፍጠር በሚያገኟቸው ኳሶች ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ።
በ40ኛው ደቂቃ ላይ አበበ ጥላሁን የመጨረሻ ሰው ሆኖ ሳለ ፍፁም ገብረማርያም ኳሱን ነጥቆት የነበረ ቢሆንም ፍፁም ያገኘውን አጋጣሚ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ሳሙኤል ሳሊሶ ከግራ መስመር ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ንስምባቢ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢልከውም በረከት በድንቅ ብቃት ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶታል ። ከሰኮንዶች ቆይታ በኋላ በድጋሚ ከቀኝ መስመር ጌቱ ሀይለማርያም ወደ ግብ ክልል ለፍፁም ያሻገረለትን ኳስ በረከት አማረ ተቆጣጥሮታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በኢትዮጵያ ቡና 1 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሰበታ ከተማዎች የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ተከታታይ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የጀመሩት ነበር ። በ47ኛው ደቂቃ ላይ ጌቱ ሀይለማርያም ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ የመታው ኳስ በበረከት ሲመለስ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በሀይሉ ግርማ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያድን የነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ በረትተ ወደ ውጪ በማውጣት የማዕዘን ምት እንዲሆን አድርጎታል ።
ተጋጣሚያቸውን በፈጠረባቸው ጫና ወደ በሜዳቸው ላይ በቁጥር በዝተው ለመቆየት የተገደዱት ቡናማዎቹ የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራቸውን በ59ኛ ደቂቃ በዊልያም ሰለሞን አማካኝነት ማድረግ ቢችሉም ዊልያም ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ምንተስኖት አሎን ማለፍ የቻለ አልነበረም ። ሰበታ ከተማዎች በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በበረከት ሳሙኤል እና በአፒያህ አማካኝነት በ63 እና 64ኛ ደቂቃ ላይ ያደረጓቸው የግብ ሙከራዎች ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም ።ሰበታ ከተማዎች ብልጫውን ወስደው የኢትዮጵያ ቡናን የኋላ ክፍል ለመፈተን ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ግን ሊሳካላቸው አልቻለም ።
- ማሰታውቂያ -
ከ70ዎቹ ደቂቃዎች መግቢያ በኋላ የቡናማዎቹ የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር ። በዚህም በ70ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ሰለሞን ለአቡበከር ናስር የሰነጠቀለት ኳስ እና አቡበከር ሳይደርስበት የቀረው ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ነበር ።የጨዋታው የደቂቃዎች መቁጠሪያ 80ኛው ደቂቃ ላይ ሲያመለክት የመሀል ተጫዋቹ እና የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን አምበል ሮቤል ተክለሚካኤል ከረጅም ርቀት ላይ ሳይታሰብ ባልታሰበ ጊዜ ካልታሰበ ቦታ ላይ የተጫዋቹን እይታ በሚያስደንቅ መልኩ ወደ ግብ የላከው ኳስ ከመረብ ላይ አርፎ የቡናማዎቹ ሁለተኛ ግብ ሆኖ ተቆጥሯል ።
ጨዋታውም ሌላ ግብ ሳይታከልበት በቡናማዎቹ የ2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 24 በማድረስ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሰበታ ተማ በበኩሉ ለሳምንታት በዘለቀበት 16ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ19ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ሰበታ ከተማ በመጪው ዕሁድ አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡናን ሲገጥም በማግስቱ ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን በተመሳሳይ ሰዓት ይገጥማል ።