በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከሰበታ ከተማ አገናኝቶ ያሬድ ባየህ ከእረፍት በፊት ባስቆጠረው ግብ አሸንፈዋል ።
ሰበታ ከተማዎች በ25ኛው ሳምንት በአዳማ ከተማ 3 ለ 0 በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ስድስት ለውጦችን በማድረግ ሰለሞን ደምሴ ፤ አንተነህ ተስፋዬ ፤ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፤ አንተነህ ናደው ፤ ሀምዛ አብዱልመን እና ቢስማርክ አፒያን በለአለም ብርሀኑ ፤ በረከት ሳሙኤል ፤ ሳሙኤል ሳሊሶ ፤ ዱሬሳ ሹቢሳ ፤ በኃይሉ ግርማ እና ንስባምቢን ሲያሰልፉ በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሰዒድ ሀሰን ፤ ከድር ኩሊባሊ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በአለምብርሀን ይግዛው ፤ እኔ ሱራፌል ዳኛቸው ተክተው ገብተዋል ።
በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ከቀን 10:00 ጀምሮ በባህርዳር ስታድየም ላይ ሲደረግ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በስድስት ነጥብ ልዩነት ላይ ሆኖ የጀመረው ፋሲል ከነማ የነጥብ ልዩነቱን ዝቅ ለማድረግ በጨዋታ ላይ ሙሉ ብልጫ ወስደው ነበር መጫወት የቻሉት ።
ሙጂብ ቃሲምን የፊት አጥቂ አድርገው የጀመሩት አፄዎቹ ደጋግመው ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ቢጥሩም የሰበታ ከተማውን ግብ ጠባቂ የፈተነ የግብ ሙከራ ለማድረግ ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በ21ኛው ደቂቃ ላይ እኪኪ አፎላቢ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ ቢልከውም ጌቱ ሀይለማርያም ተደርቦ አውጥቶታል ።
ከደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ከክለባቸው ጋር ውዝግብ ውሰጥ የነበሩት እና በአንድ ላይ ተሰብስበው ዝግጅት ሳያደርጉ ወደዚህ ጨዋታ የገቡት ሰበታ ከተማዎች ወደ ኋላ አፈግፍገው በመጫወት በተወሰኑ አጋጣሚዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃቶች ወደ ፋሲል ከነማ የግብ ክልል ለመድረስ ቢጥሩም ያን ያህል ተፅዕኖ የፈጠረ አልነበረም ።
ጨዋታው 35ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስም የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ ተቆጥሯል ። ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ሽመክት ጉግሳ በአየር ላይ ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ አምበሉ ያሬድ ባየህ ግሩም ግብ አስቆጥሯል ።
ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም ሰበታ ከተማዎች በቢስማርክ አፒያ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ያደረጉት ሙከራ በፋሲል ከተማው የግብ ዘብ ሳማኪ ሚኬል ተመልሷል ። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች በቀሩት ጊዜም አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ።
የሁለተኛውን አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች በፈጣን የግብ ሙከራ ነበር መጀመር የቻሉት ። በአጋጣሚውም ቢስማርክ አፒያ በሳጥን ውስጥ ሆኖ በተከላካኖች መካከል የደረሰውን ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል ተይዞበታል ።
የመጀመሪያውን አጋማሽ በመሪነት ያጠናቀቁት አፄዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ግቦ ለማስቆጠር የበላይነቱን ወስደው በመጫወት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ። በአጋማሹ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ውስጥም በሙጂብ ቃሲም ፤ በዛብህ መለዮ እና ኦኪኪ አፎላቢ አማካኝነት ያደረጓቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም ።
በ67ኛው ደቂቃ ላይም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሳጥኑ የቅርብ ርቀት ወደ ግብ የሞከረውን ኢላማውን የጠበቀ ኳስ ግብ ጠባቂው ሰለሞን ደምሴ ግብ ከመሆን አድኖታል ።
የሰበታ ከተማን የኋላ ክፍል መፈተናቸውን የቀጠሉት አፄዎቹ በ75 እና 76ኛው ደቂቃ ላይ በኦኪኪ አፎላቢ እና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አማካኝነት ያደረጓቸው ለግብ የቀረቡ የግብ ሙከራዎችን በጨዋታው ድንቅ የነበረው የሰበታ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰለሞን ደምሴ ግብ ከመሆን አድኗቸዋል ።
በመጨረሻም አፄዎቹ በአምበላቸውን ብቸኛ ግብ ሰበታ ከተማን 1 – 0 ረተዋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 52 አድርሶ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ ሲያደርግ ሰበታ ከተማ በበኩሉ በነበረበት 16ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሰኔ 13 ( ሰኞ ) ረፋድ 4:00 ላይ ከአዳማ ከተማ ሲጫወት ቀጥሎ 7 ሰዓት ላይ ደግሞ ሰበታ ከተማ ከሀድያ ሆሳዕና ይጫወታል ።