በ22ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የሰበታ ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በሁለቱም በኩል ግብ ሳይስተናገድበት 0 – 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
ሰበታ ከተማዎች በ21ኛው ሳምንት በድሬዳዋ ከተሣ በተረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ 11 አምሰት ለውጦትን ያደረጉ ሲሆን በምንተስኖት አሎ ፤ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፤ አንተነህ ተስፋዬ ፤ ታፈሰ ሰርካ ፤ ዱሬሳ ሹቢሳ ምትክ ለአለም ብርሀኑ ፤ በረከት ሳሙኤል ፤ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፤ ሀይለሚካኤል አደፍርስ እና ቢስማርክ አፒያን ሲያሰልፉ ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በሳምንቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረቱ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ ፀጋአብ ዮሐንስ ፤ አብዱልባሲጥ ከማል ፤ አቤኔዘር ኦቴን እና ኤፍሬም አሻሞን በመድኃኔ ብርሀኔ ፤ ወንድማገኝ ሀይሉ ፤ መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ማድረግ ችለዋል ።የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያስለመለከተን ነበር ። ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል የኳስ ቁጥጥር ሂደት በታየበት ጨዋታ ላይ ምንም እንኳን በቀኝም በግራም በኩል ባሉት ግብጠባቂዎች ላይ ጠንከር ያሉ ሙከራዎች ሲደረጉ ባንመለከትም በአንፃራዊነት ሰበታ ከተማዎች በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል ።
9ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ አፒያህ የነጠቀውን ኳስ ተጠቅሞ ከሳጥን ውጪ ያደረገው የግብ ሙከራ ለጥቃት ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ። ቀጣዩ የግብ ሙከራ ከ21 ደቂቃዎች በኋላ የታየ ሲሆን አፒያህ በድጋሚ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከው ኳስ በዳግም ተፈራ ተመልሷል ።
ጨዋታው ከወሀ እረፍት ሲመለስ ሰበታ ከተማዎች በሁለቱ መስመሮች በኩል ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን አድርገው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በሀዋሳ ከተማ በኩል በአጋማሹ የነበረው ብቸኛ ሙከራ በ38ኛው ደቂቃ ላይ በበቃሉ ገነነ የተመዘገበ ሲሆን ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ለአለም ብርሀኑ አድኖበታል ።
መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ሃይለሚካኤል አደፍርስ ጌቱ ሀይለማርያም ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ያሻገረለትን ኳስ አረጋግቶ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ዳግም ተፈራ መልሶበታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል ።
ሰበታ ከተማዎች የበላይነትን ወስደው በጀመሩት የሁለተኛው አጋማሽ ላይ በተለይም የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ላይ ከመስመር በሚሻገሩ የአየር ላይ ኳሶች በተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ግን ለማድረግ ተቸግረው ነበር ። የሰበታ ከተማ የሶስተኛው የማጥቃት ዞን የኳስ አጠቃቀም ችግሮች በተደጋጋሚ ቡድኑን ዋጋ እያስከፈሉት ካሉ እና በሊጉም የመጨረሻውን ደረጃ እንዲይዝ ካደረጉት ነገሮች እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት አንዱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ላይ የተመለከትነው ሲሆን በዚህ ጨዋታም በጉልህ የተመለከትነው ይህንኑ ነው ።
በሀዋሳ ከተማ በኩል በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ ሰፊውን ጊዜ ያጠፉ ሲሆን በተወሰኑ አጋጣሚዎች ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ቢጥሩም እንቅስቃሴያቸው ያን ያህል አደገኛ አልነበረም ።በአጋማሹ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 72ኛው ደቂቃ ላይ የተደረገ ሲሆን በሳሙኤል ሳሊሶ ከማዕዘን የተሻገረ ኳስ አግኝቶ ጠንከር አድርጎ ወደ ግብ ቢልከውም ዳግም ተፈራ አድኖበታል ።
ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ተቀይሮ የገባው ዱሬሳ ሹቢሳ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ከነ ጉዳቱ በመጫወት ላይ የነበረው ዳግም ተፈራ በድንቅ ብቃት ግብ ከመሆነሰ አግዶታል ።
84ኛው ደቂቃ ላይም ጌቱ ሀይለማርያም ከግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ያሻገረውን ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ በግንባር መግጨት ቢችልም ኳሱ ለጥቂተ ወደ ውጪ ወጥቷል ።
በመጨረሻም ጨዋታው ያለ ግብ ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ነጥቡን 35 በማድረስ ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍል ሲል ሰበታ ከተማ በበኩሉ ነጥቡን ወደ 14 ማሳደግ ቢችልም አሁንም በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛል ።
በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 3 ( ረቡዕ ) ረፋድ 4:00 ላይ ሰበታ ከተማ ጅማ አባጅፋርን ሲገጥም ከሁለት ቀናት በኋላ ግንቦት 5 ( አርብ ) በተመሳሳይ ሰዓት ሀዋሳ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ ይጫወታል ።