በሊጉ አስረኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ውሎ ከምሽት 12 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው ጨዋታ አዳማ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ሰበታ ከተማን ማሸነፍ ችሏል ።
አዳማ ከተማ በዘጠነኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ በተጠቀሙት አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የገቡ ሲሆን በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ በወልቂጤ ከተማ በተሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው ቋሚ አስራአንድ ቢያድግልኝ ኤልያስ ፤ ሀምዛ አብዱልመን ፤ ፍፁም ገብረማርያም ፤ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ንታንቢ ክሪስቶዝም በወልደአማኑኤል ጌቱ ፤ ታፈሰ ሰርካ ፤ በሀይሉ ግርማ ፤ አክሊሉ ዋለልኝ እና ዘካርያስ ፍቅሬን ቀይረው ጨዋታውኝ ጀምረዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እምብዛም ለአይን ሳቢ ፉክክር ያልታየበት ነበር ። በጨዋታው አዳማ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና በማጥቃቱ ረጠድ የበላይነት አስመልክተው ነበር ። በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች ቿሚነጠሹ ኳሶች በፍጥነት ወደ ፊት በማለፍ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በግብ ሙከራ ያልታጀበው የምሽቱ ጨዋታ በ23ኛ ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ግብ አስተናግዷል ። የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው በተከታታይ የተሞከሩበትን ኳሶች ማዳን ከቻለ በኋላ ሃይለሚካኤል አደፍርስ ያደረገውን ሙከራ ግን መመለስ ሳይችል ቀርቶ ሰበታ ከተማዎች ቀዳሚ ያደረጋቸውን ግብ ማግኘት ችለዋል ።
ከግቡ በኋላ አዳማ ከተማዎች መልስ ለመስጠት በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ግብ ማግኘት ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል ።
የሁለተኛው ኢጋማሽ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የፋሲል ተካልኝ ልጆች አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ማግኘት ችለዋል ። ወልደአማኑኤል ጌቱ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ 51ኛ ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ የጨዋታውን ውጤት ወደ 1 ለ 1 ቀየረው ።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም ወደ ፊት ሄደው ጫና በመፍጠሩ ረገድ ደከም ብለው ታይተዋል በአንፃሩ ሰበታ ከተማዎች በሚነጠቁ ኳሶች በፈጣን ሁኔታ በመላክ ወደ ፊት በመሄድ ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ነገር አሳይተው ነበር ።
79ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አብዲሳ ጀማል በመልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ በሰበታ ከተማ ግብ ላይ በማስቆጠር አዳማ ከተማዎችን ከመመራት ወደ መሪነት የቀየረ ግብ አስቆጠረ ። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የነበረው የሰበታ ከተማ ግብ የማግኘት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታ ተፈፅሟል ።
ውጤቱን ተከትሎም አዳማ ከተማ ነጥቡን 15 በማድረስ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሽንፈት የገጠመው ሰበታ ከተማ በ7 ነጥብ በነበረበት 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።