ሲዳማ ቡና በአምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ 11 ዳዊት ተፈራን ብቻ በመቀየር ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ዮሴፍ ዮሀንስ ፤ አሜ መሀመድ እና አብዲሳ ጀማልን ቀይረው በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግብ ለማስተናግድ 3 ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጁበት ። ሀብታሙ ገዛኸኝ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ግርማ በቀለ ሲዳማ ቡናን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጠረ ። ከግቧ መቆጠር በኋላ አዳማ ከተማዎች የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ መጫወት ችለዋል በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሙከራዎችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ግብ ሲደርሱ የነበሩር አዳማ ከተማዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ 23 ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደዋል ። በደቂቃው ላይ አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክረው የግቡ ቋሚ መልሶበት ወዲያው ያገኘው አቡበከር ወንድሙ በድጋሚ ወደ ግብ ቢሞክረውም በተክለማርያም ሻንቆ በቀላሉ ተይዞበታል ። ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች 32ኛ ደቂቃ ላይ አቻ የሚያደርጋቸውን ግን አገኙ ። ሚሊዮን ሰለሞን ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ጎበና በግንባር በመግጭት አስቆጠረ ። በቀሩት የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና በተሻለ ወደ ግብ ቢያመሩም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ የታየበት ነበር ። በሁለቱም በኩል በተወሰኑ አጋጣሚዎቾ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶች ቢታዩም የግብ ሙከራዎችን ግን በቀላሉ ማድረግ አልቻሉም ።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ግን ቀደም ብሎ ከነበረው የተሻለ እንቅስቃሴ በሜዳ ላይ የታየ ሲሆን ከሁለቱም በኩል የአሸናፊነቱን ግብ የሚያስቆጥር ተጫዋች ማግኘት ሳይቻል ጨዋታወሰ በአቻ ውጤት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎም ከጨዋታው በፊት በእኩል ስድስት ነጥብ ላይ የነበሩት ሁለቱ ክለቦች ነጥባቸውን ሰባት ሰባት አድርሰዋል ።