በ14ኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተካሄደው የሲዳማ ቡና እና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ በሲዳማ ቡና 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።ሲዳማ ቡና በ14ኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን ግርማ በቀለ እና ብሩክ ሙሉጌታ ጊት ጋትኩትን እና ቴዎድሮስ ታፈሰን ተክተው የገቡ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ደግሞ ሰበታ ከተማን በሰፊ ውጤት ሲረቱ በነበረው ቋሚ አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ኳሱን ይዘው በመጫወት ወደ ማጥቃቱ ሶስተኛ ዞን ለመግባት ጥረቶችን ያደረጉበት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ደግሞ ኳሶችን በረጃጅም ወደ ፊት በመላክ የግብ አማራጮችን ለማግኘት የሞከሩበት ነበር ።በጨዋታው 9ኛ ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ በረጅም የደረሰውን ኳስ በቀኝ መስመር በኩል ሆኖ ወደ ግብ ያሻገረውን ኳስ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ለማግኘት ቢጥርም ኳሱ ላይ ለመድረስ ሳይችል ቀርቷል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ሪችሞንድ በድጋሚ ከእንዳለ የደረሰውን ኳስ ጠንከር አድርጎ ባለመምታቱ በሲዳማ ቡና ተከላካዮች ተመልሶበታል ።
በ24ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ከቀኝ መስመር አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት ሮቤል ግርማ ወደ ግብ ሞክሮት የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ። ከውሀ እረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ሲዳማ ቡናዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ቢችለም ወደ አዲስ አበባ የግብ ክልል አልፈው ለመግባት ተቸግረው ነበር ።34ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቃት ወደ ውጪ የወጣ ሲሆን ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ሳሙኤል አስፈሪ ኳስ ለማቀበል በሚሞክርበት ጊዜ ሀብታሙ ገዛኸኝ ነጥቆት ለይገዙ ቦጋለ አቀብሎት ይገዙ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በዳንኤል ተሾመ ተመልሶ የማዕዘን ምት ሆኗል ። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለግብ ተጠናቋል ።
ሁለተኛው በጥሩ የጨዋታ ፍጥነት የጀመረ ሲሆን በሲዳማ ቡናም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በፈጣን ወደ ግብ ለመድረስ እንቅስቃሴዎች የተደረጉበት ነበር ። በአንፃራዊነት ሲዳማ ቡናዎች በተሸላ ኳሱን ይዘው ወደ ግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉበት ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ በኩል በፈጣን ሽግግር ወደ የሲዳማ ቡናን ተከላካዮች ለመፈተን ችለው ነበር ።በ59ኛ ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ከሙሉአለም መስፍን የደረሰውን ኳስ ለይገዙ ቦጋለ በማቀበል ነፃ ሆኖ በመገኘት መልሶ የተቀበለውን ኳስ በአዲስ አበባ ከተማ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ። ከግቡ በኋላ ሲዳማ ቡናዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት እና በጥሩ ቅብብሎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉ ሲሆን በመመራት ላይ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ውጤታማ ካልሆኑት ፈጣን ሽግግሮቻቸው በተጨማሪ ከቆሙ ኳሶች ግብ ለማግኘት ሞክረዋል ። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች ወደ ፊት ተጭነው ለመጫወት የጣሩ ሲሆን በነዚህ አጋጣሚዎች ሲዳማ ቡናዎች በፈጣን ወደ ግብ ለመድረስ የቻሉባቸውን ዕድሎች የፈጠሩ ሲሆን በተለይም 82ኛ ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከመሀል የተሰነጠቀለትን ጥሩ ኳስ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ከሽፎበታል ።
- ማሰታውቂያ -
በሲዳማ ቡና በኩል በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በፍሬው ሰለሞን አማካኝነት በተከታታይ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም ኳስ እና መረብን ግን ማገናኘት አልቻሉም ነበር ። ወደ ሲዳማ ቡና የግብ ክልል ደርሰው የግብ ሙከራዎች በማድረጉ ረገድ አይናፋር የሆኑት የመዲናዋ ክለብ ተጫዋቾች በ90+2 ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ። በአጋጣሚው ከኤልያስ አህመድ ወደ ግብ የተመታውን ኳስ ያገኘው ሪችሞንድ ኦዶንጎ ኳሱን ተቆጣጥሮ ወደ ግብ መሞከር ቢችልም ተክለማርያም ሻንቆ ወጥቶ አድኖበታል ። በመጨረሻም ሲዳማ ቡና ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ መውጣት ችሏል ።ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 22 በማድረስ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በ10 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል ።
በ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና ሀድያ ሆሳዕናን አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚገጥሙ ይሆናል ።