በትላንትናው ዕለት ጅማሮዉን ባደረገዉ የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ከሰዓት 10:00 ሰዓት ላይ ተገናኝተው ጨዋታቸውን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
ድንቅ ፋክክርን ያስመለከትን የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ገና ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ በሙከራ የታጀበ ነበር ፤ በዚህም በ7ኛዉ ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል ይገዙ ቦጋለ ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ ሳልሃዲን ሰይድ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በድሬዳዋዉ ግብ ጠባቂ ፍሬዉ ጌታሁን ጥረት ግብ ከመሆን ቀርታለች።
በሁለቱም ክለቦች በኩል ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን በተመለከትንበት የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ሁለቱም ቡድኖች በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የገብ ክልል ሲደርሱ ተስተውሏል። በተለይ የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር ጫናቸዉ እየበረታ የመጡት ሲዳማ ቡናዎች በ31ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠስ ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
በዚሁ ደቂቃ ላይም በግራ መስመር በኩል ሳልሃዲን ሰይድ ያሻገረዉን ኳስ እንዳለ ከበደ ወደ ግብነት ቀይሮ ሲዳማ ቡናዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ግቡን ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ ጥረት ሲናደርጉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከ8 ደቂቃዎች በኋላ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም አብዱለጢፍ መሐመድ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ እንየዉ ካሳሁን በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። በዚህም አንድ አቻ በሆነ ዉጤት ሁለቱም ክለቦች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በተመጣጣኝ ፋክክር በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም 47ኛ ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ዳግም መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የድሬዳዋዉ ተከላካይ እንየዉ ካሳሁን አስራ ስድስት ከሀምሳ ዉስጥ ኳስ በእጁ በመንካቱ ምክንያት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ሳልሃዲን ሰይድ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ዳግም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ተጭነዉ መጫወት የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ በ50ኛዉ እና በ58ኛዉ ደቂቃ ላይ በአብዱለጢፍ መሐመድ እና ጋዲሳ መብራቴ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር ግን ተቸግረው ነበር ፤ ነገር ግን በይበልጥ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በ64ኛዉ ደቂቃ ላይ ዳግም አቻ መሆን ችለዋል። በዚሁ ደቂቃ ላይም አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ ከርቀት ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታዉ መመለስ ችሏል።
በዚህም በተለይ ከ75ኛዉ ደቂቃ በኋላ በይበልጥ ተጭነዉ በመጫወት ዳግም መሪ መሆን የሚችሉበትን ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራ በግብ አስቆጣሪዉ እንዳለ ከበደ እና ሳልሃዲን ሰይድ አማካኝነት ማድረግ የቻሉት ሲዳማ ቡናዎች ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በተቃራኒው ወደራሳቸዉ የግብ ክልል በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎችም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይም የሲዳማ ቡናዉ ተከላካይ ጊት ጋትኮት ብሩክ ቃልቦሬ ላይ በሰራዉ ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት በተመሳሳይ የድሬዳዋ ከተማዉ ኤልያስ አህመድ ከዳኛ ጋር በገባዉ ሰጣገባ ምክንያት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
በቀጣይ ሲዳማ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና ጋር የሚጫወቱ ሲሆን በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ከአዲስ አዳጊዉ ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የሚገናኙ ይሆናል።