በ16ኛው ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት የተደረገው የሲዳማ ቡና እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ከእረፍት በፊት በተቆጠሩ ግቦች አንድ ለአንድ ተጠናቋል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በ15ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ከነበረው ቋሚ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ የገቡ ሲሆን በቴዎድሮስ በቀለ ፣ ገዛኸኝ ደሳለኝ ፣ ያብቃል ፈረጃ እና ሚኪያስ መኮንን ምትክ አበበ ጥላሁን ፣ ወንድሜነህ ደረጄ ፣ አማኑኤል ዮሀንስን እና ዊልያም ሰለሞንን ያሰለፉ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ በሳምንቱ ሀድያ ሆሳዕናን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 አንድ ለውጥ ብቻ ያደረጉ ሲሆን ብሩክ ተስፋዬ ቴዎድሮስ ታፈሰን ተክቶ በጨዋታ ላይ መሰለፍ ችሏል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሱን ከኋላ መስርተው ለመውጣት ጥረቶችን በማድረግ የጀመሩ ሲሆን በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ቡናማዎቹ ኳሱን በሚይዙበት ጊዜ ጫና በመፍጠር የሚነጠቁ ኳሶችን በፍጥነት ወደ ፊት መስመር በመውሰድ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ያደረጉበት ነበር ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በመሀል ላይ ኳሱን በቀላሉ ተቀባብለው ለመውጣት ቢቸገሩም በግራ መስመር በኩል በአስራት ፣ ዊልያም እና አቡበከር ናስር አማካኝነት ጥሩ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ፊት ለማለፍ ጥረቶችን አድርገው ነበር ። ምንም እንኳን በዚህ መስመር ቡናማዎቹ ጫና ለማድረግ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የሲዳማ ቡናን የተከላካይ ክፍል አልፈው ወደ ሳጥን ለመግባት ግን ቀላል አልሆነላቸውም ።
- ማሰታውቂያ -
በ10ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ሰለሞን በአቡበከር ናስር እና ሮቤል ተክለሚካኤል በኩል አልፎ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ ሞክሮት የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሶበታል ።
በ26ኛው ደቂቃ ላይ ሲዳማ ቡናዎች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል ።
ሀብታሙ ገዛኸኝ በግራ መስመር ወደ ሳጥን ይዞ የገባውን ኳስ ፍሬው ተቀብሎ በአንድ ንክኪ ለመሀሪ መና አቀብሎት መሀሪም ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ በሁለቱ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ሀይሌ ገብረትንሳይ እና ወንድሜነህ ደረጄ እግሮቻቸው መሀል አልፎ ከመረብ ላይ አርፏል ።
ኢትዮጵያ ቡናዎችም ከውሀ እረፍት መልስ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ለተቆጠረባቸው ግብ መልስ ሰጥተዋል ። አቡበከር ናስር በሳጥኑ ቅርብ ርቀት በግራ አቅጣጫ ላይ በራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት ያገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ መቶ በማስቆጠር የጨዋታውን ውጤት ወደ አንድ እኩል መለወጥ ችሏል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ቡናማዎቹ ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት የሲዳማ ቡናን የተከላካይ መስመር አልፈው ለመግባት ጥረቶችን ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመቅረብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር ።
በ38ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ለሀብታሙ ገዛኸኝ ጥሩ ኳስ አቀብሎት ፈጥኖ ወደ ሳጥን በመግባት ዳግም በእግሩ ስር የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በአቤል ማሞ የተመለሰበት ሲሆን በ43ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በጨረቃዋ ውስጥ ፍሬው ሰለሞን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ዳዊት ወደ ግብ ልኮት በአቤል ማሞ ሲመለስ በቅርብ የነበረው ግብ አስቆጣሪው መሀሪ የተመለሰውን ኳስ ማግኘት ቢችልም ለጥቂት ወደ ውጪ ወቶበታል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በአንድ እኩል ውጤት ተጠናቀቀ ።
የጨዋታው የሁለተኛው አጋማሽ ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳሱን በበላይነት ይዘው በተለይም በመስመሮች በኩል ወደ ሳጥን ገብተው የግብ ዕድሎችን ለማግኘት የጣሩበት እንዲሁም ሲዳማ ቡናዎች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉበት ነበር ።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ ሆነው ቢታዩም በቀላሉ ወደ ግብ ቀርበው የግብ ሙከራዎች ለማድረግ በእጅጉ የተቸገሩ ሲሆን ለዚህም የሲዳማ ቡና የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ተጠቃሽ ምክንያት ነበር ።
ቡናማዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ተክለማርያም ሻንቆን የፈተነ የግብ ሙከራ ማድረግ የቻሉት በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሲሆን እሱም 55ኛው ደቂቃ ላይ ሀይሌ ገብረትንሳይ በቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን ገብቶ ለማቀበል የላከው ኳስ በጊት ጋትኩት ሲመለስ መልሶ አግኝቶ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ሲሆን ኳሱም በግብ ጠባቂው ተመልሷል ።
በሲዳማ ቡና በኩል ተደጋጋሚ ኳሶችን በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ፊት ይዘው ማለፍ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም በሶስተኛው የማጥቃት ክፍል ላይ ሲደርሱ የነበራቸው የኳስ ቅብብል በቀላሉ በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ይከሽፍ ነበር ።
ሲዳማ ቡናዎችም በአጋማሹ ለግብ የቀረበ የግብ ሙከራ ያደረጉት በአንድ አጋጣሚ ሲሆን 65ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከፍሬው ሰለሞን በግሩም ሁኔታ የደረሰውን ኳስ ከአቤል ማሞ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ግብ የመታው ኳስ በቋሚው ተመልሷል ።
በመጨረሻም የጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሌላ ግብ ሳይስተናገድበት አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 26 ማድረስ ቢችልም በደረጃው ላይ ለውጥ ሳያደርግ 5ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ነጥቡን 21 በማድረስ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።
በ17ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ማክሰኞ ቀን 9 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲገጥም ሲዳማ ቡና በበኩሉ በመጪው ሀሙስ በተመሳሳይ ቀን 9 ሰዓት ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር የሚጫወት ይሆናል ።